ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ነው ያጠፉት ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 2/2010) ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን በምርመራ ማረጋገጡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነሩ ከሌሎች ሃላፊዎች ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ ኢንጂነሩ ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው መረጃዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻ ሰአት  ያደረጓቸው የስልክ ልውውጦችም ሆኑ በመጨረሻ አካባቢ ያሳዩት የነበረው ባህሪ ራሳቸውን ለማጥፋታቸው ማሳያ ናቸው ሲል በሪፖርቱ ላይ ተመልከቷል።

የምርመራው ሪፖርቱን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች በመሰንዘር ላይ ናቸው።

በተደጋጋሚ ይፋ ይሆናል የተባለው የኢንጅነር ስምኘው አሟሟት ጉዳይ ዛሬ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል።

ይህንንም አስመልክቶ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተኮላ አይፎክሩ እና የወንጀል ምርመራ ኃላፊው ኮማንደር አለማየሁ ኃይሉና የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በጋራ ብሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ኢንጂነሩ ከመሞታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በመስቀል አደባባይ አካባቢ መታየታቸውን በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ሃላፊዎቹ እንዳቀረቡት ሪፖርት ከሆነም በማግስቱ ማለዳ 12.45 ላይ ወደቢሯቸው አቅንተው ነበር የተባሉት ኢንጂነር ስመኘው ራሳቸውን ከማጥፋታቸው ከጥቂት ደቂቃ በፊት ከልጃቸው ጋር መገናኘታቸውም ታውቋል፡፡

ራሳቸውን እንዳጠፉ መረጃው ደርሷቸው በስፍራው ተገኝተዋል የተባሉት ፖሊሶችም ኢንጂነሩ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ማግኘታቸውን ብሎም ለፖሊስ ኮሚሽነሩ ሪፖርት ማቅረባቸውንና የፖሊስ ኮሚሽነሩ በስፍራው መድረሳቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ተቆልፎ ነው የተገኘው የተባለው የኢንጂነሩ ተሽከርካሪ የኋላ መስኮትም የተሰበረው የሰውየውን ሕይወት ለማትረፍ በተወሰደ ርምጃ እንደሆነም ገልጸዋል።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራም ኢንጂነሩ ራሳቸውን በጥይት መምታታቸውን ማረጋገጡንና ጥይቱም በተሽከርካሪው ውስጥ መገኘቱን አረጋግጧል።

በተሽከርካሪው ውስጥ የተገኙት ወረቀቶችም የስራቸውን ብዛት ከማሳየት ውጪ የያዙት ሌላ መረጃ አለመኖሩንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

ፖሊስም እነዚህንና ሌሎች የግለሰቡን ወቅታዊ መረጃዎች መነሻ በማድረግም ኢንጂነሩ ራሳቸውን በራሳቸው ስለማጥፋታቸው አረጋግጫለሁ ሲል ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡

የቀብራቸው ዕለት ቤታቸውን ለመዝረፍ የተደረገው ሙከራም ሆነ ግለሰቡ በሌሎች ተገድለው ይሆናል በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎችም ሃላፊዎቹ የስርቆት ሙከራው ተራ ስርቆት መሆኑንና ኢንጂነሩ በሌሎች እጅ ሳይሆን ራሳቸውን በራሳቸው ስለማጥፋታቸው የተገኘው መረጃ በቂ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢንጅነሩ የምርመራ ውጤት በዚህ መልኩ ለሕዝብ ይፋ ይሁን እንጂ ሌሎች መረጃዎችን አሰባስቦ ምርመራው ወደፊትም እንደሚቀጥል ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል።

የሃላፊዎቹ ሪፖርት ይህን ያመልክት እንጂ ኢንጂነሩ ራሳቸውን ገድለዋል በሚል የተሰጠው መረጃ በሕዝቡ ዘንድ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል።