በሃረር ከተማ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች በፖለቲካና በኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠየቁ

በሃረር ከተማ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች በፖለቲካና በኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠየቁ
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) በከተማዋ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች ነሃሴ 25 ቀን 2010ዓም በኢሚር አብዱላሂ አዳራሽ ባካሄዱት ስብሰባ፣
የሐረር ከተማ የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች የአቋም መግለጫ ፣ “በህገ መንግስቱ የተረጋገጠልን በየትኛውም የሐገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብታችን ሳይሸራረፍ እንዲከበር እንታገላለን፡፡” ሲሉ ጠይቀዋል።
ተወላጆቹ ፣ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸው፣ በፅኑ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ፍቅር ሀገራቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚሉትን ውድ ኢትዮጵያዊ ጀግኖቻችንን እየመረጡ መግደል ይቁም ብለዋል፡፡
በሐረሪ ክልል ባለው የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ፍትሀዊ ተሳትፎ እንዲኖር፣ በተለይ በንግዱ ኢኮኖሚያዊ የውድድር ሜዳ በነፃነት መወዳደር እንዲችል ምቹና ፍትሐዊ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከፍተኛ የስራ ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰባቸው ወጣቶች ህጋዊ ሆነው የሚሰሩበትን ቦታ መንግስት እንዲያመቻችላቸውና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ፣ በሐረሪ ክልል ተወልደው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በቋንቋ መስፈርት ምክንያት በችሎታቸው እንዳይሰሩና ህዝብና መንግስትን እንዳይጠቅሙ ትኩረት የተነፈጋቸው ምሁራን የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ጠይቅዋል።