በሰላም አስከባሪነት የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላቶች ምዝበራ እንደተፈጸመባቸው አስታወቁ። ጉዳዩንም ለጠቅላይ ሚንስትሩ እና ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀዋል።

በሰላም አስከባሪነት የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላቶች ምዝበራ እንደተፈጸመባቸው አስታወቁ። ጉዳዩንም ለጠቅላይ ሚንስትሩ እና ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀዋል።
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 02 ቀን 2010 ዓ/ም ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፈቃጅነት አፍሪካን በመወከል በጎረቤት አገራት ሰላም ለማስከበር የተሰማሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተለያዩ ምዝበራዎች ሲፈጸምባቸው መቆየቱን የሰራዊቱ አባላት ለመንግስት እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተዋል።
በመንግስት የተሰጣቸውን ግዴታዎች ከመወጣት በተጨማሪ የአገራቸውን ልማት በማገዝ ሁለተናዊ አስተዋጾ ሲያደርጉ ቢቆዩም፤ ከቤተሰቦቻቸው ቀንሰው ያዋጡት ገንዘብ መዘረፉን ሲሰሙ ማዘናቸውንና ጉዳዩ ተጣርቶ በአጥፊዎቹ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ በጻፉት ደብዳቤ ”ከተሰጠን የአገር ውስጥ ግዳጅ ውጪ በሱዳንና በሶማልያ የሰላም ማስከበር ግዳጃችንን በአግባቡ እየተወጣን መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን ግዳጅ ጨርሰን ወደ አገር ቤት ሰንመለስ በተመድ በዶላር ከሚሰጠን ገንዘብ ላይ ከመሰመራዊ መኮንኖች 53%፣ ከከባማዎች 56%፣ ከተራ ወታደሮች ደግሞ 60% እየተቆረጠ ይሰጠን ነበር” ብለዋል።
ይህም ማለት ለአንድ ዓመት በሰላም አስከባሪነት የቆየ መኮንን ግማሽ ሚሊዮን ብር በዶላር ተመንዝሮ እንደየወቅቱ የምንዛሪ መጠን ቢደርሰውም፣ የዚህ ብር መጠን 53% መከላከያ ላልታወቀ ምክንያት ቆርጦ ይወስደዋል፡፡ በዚህ መሠረት 235,000 ሺ ብር የሰላም አስከባሪው አባሉ ሲወስድ፣ ቀሪውን 265,000 መከላከያ እንዲወስድ ይደረጋል። መከላከያ ከግማሽ በላይ ገንዘባችንን ወስዶ የት እንደሚያስገባው አይታወቅም ሲሉ የሰራዊቱ አባላት በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
ሰራዊቱ ይህን ቅሬታ ሲያቀርብ የቆየ ቢሆንም ”ገንዘቡ ለመከላከያ ፋውንዴሽን ገቢ እንደሚሆንና፤ ኮንደሚኒየም ተሰርቶ ለሰራዊቱ በእጣ እንዲሠጥ እናደርጋለን።” የሚል ምላሽ ከአመራሮቹ ቢሰጣቸውም፣ እስከዛሬ ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልተደረገም። ይህም ሆን ተብሎ ወታደሩ በችግር ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ የተሸረበ ሴራ መሆኑን ይናገራሉ።
“በብዙ ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የመሳሪያ ኪራይ ገቢ ከተመድ ለሀገራችን እንዳለ እናውቃለን። ነገርግን ይህ ሁሉ ገቢ እስካሁን የት እንደገባ አይታወቅም። ለሰራዊቱም ምን እንደተሠራ በግልፅ አይነገረውም፡፡ ይህን ጥያቄ ያነሱ የሰራዊቱ አባላት ይታሰራሉ። ይህን ፍራቻም የተወሰኑት የተሰጣቸውን ገንዘብ ተቀብለው ይክዳሉ። ወይም በበቃኝ በመልቀቅ ተቃውሞዋቸውን ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት ግልጽነት ያለው አሰራር እንደሚሰፍን መንግስት በመግለጹ ጉዳያቸው በገለልተኛ ኮሚቴ” ይታይልን ብለዋል።
አክለውም “የሰላም ማስከበር ምልመላው ከግዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ መጥቷል። በተለይ ሲቪሎች ታጋይ እየተባሉ የሰራዊት ኮታ እየተሰጣቸው ይገባሉ። የህወሃት ታጋዮች እየተባሉ በተለያየ ጊዜ የሰራዊቱን ኮታ እየወሰዱ ታጋይ ያልሆኑም ጭምር ዘመድ አዝማድ እየተጠራሩ ከህግ ውጪ ተሰርቷል። ከተመድ የደረጃ መስፈርት ውጪ ብቃት የሌላቸው የትግራይ ታጋዮች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋን መናገር የማይችሉ ታዛቢ ተብለው በደቡብ ሱዳን አብዬ ግዛት ተሰማርተዋል፡፡ በታጋይ ስም የህወሃት ታጋዮች ተለይተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ፍታሃዊነት የለውም።” በማለት ጽፈዋል።
ከሰራዊት አባላት ከ15 ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ለስፖርት እየተባለ እንደየደመወዝ መጠን ገንዘባችን ይቆረጣል። ይህ የብር መጠን በአንድ ወር ብቻ ከጠቅላላ ሰራዊቱ የሚሰበሰበው ከ8,000,000 (ከሰምንት ሚሊየን ብር) በላይ ነው። ነገር ግን በመከላከያያ ስር ላሉ የስፖርት ቡድኖች በወር የሚከፈላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ተገዝተው ይህንን ያህል ገንዘብ በወር አይጨርሱም፡፡ ይህንንም ጥያቄ ስንጠይቅ አደገኛ ማስጠንቀቂያ ያለው መልስ ስለተሰጠን ዝም ብለን ቆይተናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከውስጥ አዋቂዎች ለደደቢት እግር ኳስ ቡድን እየተቀነሰ እንደሚሰጥ እንሰማለን ይህ ትክክል አይደለም ይጣራልን ሲሉም ጠይቀዋል።
“ለዓባይ ግድብም እስካሁን ያለማቋረጥ እያዋጣን ቆይተናል፣ ሌቦቹ ስለተጋለጡ ገንዘባችንን የበሉት ታውቀዋል። ከኛ ጋር ሲሰሩ የነበሩ የወታደር ማሊያና የድርጅት ማለያ ለብሰው ገዝግዘውናል። ጉዳዩን በጥሞና እየተከታተልነው፣ ሲሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ላብ እንዲመለስ መደረግ አለበት። “ ሲሉ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ፣ ለመከላከያ ሚንስቴር፣ ለመከላከያ ሚንስቴር ኢታማዦር ሹም፣ ለኢህአዲግ ጽ/ቤት፣ ለመረጀና ደህንነት እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን በኢሜል አሳውቀዋል። ኢሳት በሰላም ስከባሪ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ እንደሚፈጸም የወታደራዊ ምንጮችን በመጥቀስ በተደጋጋሚ መዘገቡ ያታወሳል።