በአባይ ግድብ ዙሪያ ከፍተኛ ጥበቃ ማድረግ ተጀመረ

ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለኢሳት የደረሰው የደህንነት መረጃ እንዳመለከተው ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው  ቻይና እና ሩሲያ ሰራሽ ራዳሮች ሰሞኑን በአካባቢው ተተክለዋል።

መንግስት  ማንኛውንም አይነት ድንገተኛ የአየር ወይም የሰርጎ ገቦች ጥቃት ለመከላከል ዘመናዊ ራዳሮችን ከመትከል በተጨማሪ  የተወሰኑ የአጋዚ ክፍለ ጦር አባላት በአስችኳይ ወደ አካባቢው እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል። በፌደራል ፖሊስ ሲደረግ የነበረው ጥበቃ በመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲጠናከር ያደረገው መንግስት ፣ በሻለቃ አበራ ወረታው አዛዥነት የሚመራው የምእራብ እዝ የ44ኛ ዳሎል ክፍለ ጦር አራተኛ ሪጂመንት በቤንሻንጉል እንዲቀመጥ ተወስናል።

በደቡብ ሱዳን ያለው ጦር የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኝም አብዩታዊ ዴሞክራሲ እና ወታደራዊ አመራር የሚል ርእስ ያዘለ የመወያያ ጽሁፍ ተዘጋጅቶ በ ስልጠና ዋና መምሪያ. ሌ/ጅኔራል  ታደሰ ወረደ የሚመራ ቡድን ወደ አብየ አቅንቷል፡፡

ኢሳት የደረሱትን ሙሉ ወታደራዊ የደህንነት መረጃዎች ለአገር ደህንነት ሲባል ይፋ ከማውጣት መቆጠቡን ለመግለጽ ይወዳል። የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምኦን ኢትዮጵያ ምንም አይነት ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገች አይደለም በማለት ሰሞኑን መግለጫ ቢሰጡም፣ ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል እንቅስቃሴዎችን ጀምራለች።

በሌላ ዜና ደግሞ  የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ  የማሸሻያ እርምጃ እንድታደርግ መጠየቁ ታውቋል። የግብጽ መንግስት ያቀረበው ጥያቄ የግድቡ ከፍታ ከነበረበት 145 ሜትር ወደ 100 ሜትር ዝቅ እንዲል፣ 74 ቢሊዩን ሜትር ኩብ ውሃ እንደሚይዝ የሚጠበቀው አዲሱ ሀይቅ  ከ 32 እስከ  40 ቢሊዩን ሜትር ኩብ ውሀ እንዲቀንስ መጠየቁን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የሀይል አቅርቦቱም ወደ 3000 ሜጋ ዋት እንዲቀንስ የግብጽ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል።