ሰማያዊ ፓርቲ <<በአባይ ወንዝ ላይ የተጀመረው ግድብ ከሐገራዊ ጠቀሜታው ይልቅ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን እድሜ ለማራዘም የታለመና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚደለቅ ከበሮ ነው>> አለ።

ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰማያዊ ፓርቲ ፦<<እነሱ ከ አባቶቻቸው አይበልጡም፤ እኛም ከ አባቶቻችን አናንስም>> በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ወረራና ደባ መፈፀም የጀመረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በአባይ ላይ ግድብ ለመስራት ከመነሳቷ እጅግ በርካታ አመታት በፊት ጀምሮ መሆኑን  በመጥቀስ ሀገራችን ከግብፅም ሆነ ከሌሎች የተቃጣባትን ተደጋጋሚ ወረራዎች በመመከትና ጠላቶቿንም ድባቅ በመምታት ነፃነቷን ጠብቃ መኖሯ ለጠላቶቿ መራር የሆነ እውነት ነው ብሏል።

ግብፅ በ ኢትዮጵያ ላይ  ግልፅ እና ስውር ደባ የምትፈፅመው ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም የማትችል ደካማ ሐገር እንድትሆን ለማድረግ ነው ያለው  ሰማያዊ ፓርቲ፤ይህ ጥረቷ ግን ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከመሞከሯ ውጭ የምኞቷን ያህል አልተሳካላትም ብሏል።

<<ግብጽ እኛን ኢትዮጵውያንን እርስ በእርሳችን በማናከስ በጦርነትና በክፍፍል ተጠምደን ወንዞቻችንን የመጠቀም አቅም በማሳጣት ለዘለዓለም ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና መኖር ትፈልጋለች>>ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ << ይህ ካልተሳካላት ቀጥተኛ ወረራ በመፈፀም የወንዞቻችን ምንጮች ለመቆጣጠር እንደምትመኝ የየዘመናት ሙከራዎቿ ያመላክታሉ>>ብሏል።

ሰማያዊ ፓርቲ በማያያዝም -በአባይ ወንዝ ላይ የተጀመረው ግድብ ከሐገራዊ ጠቀሜታው ይልቅ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን እድሜ ለማራዘም የታለመና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚደለቅ ከበሮ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል ብሏል።

<<የግድቡ ሥራ የገዥውን ፓርቲ የተለየ አሣቢነትና ተቆርቋሪነት የሚያሳይ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ልፈፋ ከተራ ጩኸት በዘለለ የዜጎችን ልብ የሚያማልል አይደለም፡፡>>ያለው ፓርቲው፤ << በአንፃሩ ከገዥው ፓርቲ አመለካከት ውጭ ያሉ ዜጎችን የግድቡ ሥራ የማይመለከታቸው አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው የወሬ ክምር ልብን የሚሰብር ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡>>ሲል ተችቷል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ክብርና ኩራት መሠዋት ለዜጎችም ጥቅም መጠበቅ እነማን ምን እንደከፈሉና እንደሚያስቡ ለታሪክ በመተው ሃገርን መክዳትና መጥላትን በሌሎች ላይ ለመለጠፍ የሚደረገው ሩጫ ግን እንዲታሰብበት እንመክራለን ሲልም ፓርቲው ምክሩን አስተላልፏል።

ከዚህም ባሻገር <<የግድቡ ሥራ ከስም አወጣጥ ጀምሮ የፕሮጀክቱ አነዳደፍ፤ የፋይናንስ አሰባሰብ፣ ግንባታውን የሚያካሂዱ ድርጅቶች አመራረጥና ሌሎችም ጉዳዮች እጅግ ግልፅነት የጎደላቸውና ባለቤትነታቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥቆ ለተወሰኑ ቡድኖች በተለይም ለገዥው ፓርቲ ፍላጎት ማሳኪያ እየዋለ መሆኑ ቀርቶ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሚያስማማ ሁኔታ እንዲካሄድ ፓርቲያችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡>>ሰማያዊ ፓርቲ ጥያቄ አቅርቧል።

ፓርቲው መግለጫውን ሲያጠቃልልም፦<<አሁን የተፈጠረው ውጥረት በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ እያሳሰብን ነገር ግን ግብፅ ይህን አልቀበልም በማለት ፍላጎቷን በሃይል ለማስፈፀም የምትፈልግ ከሆነ የአባቶቻችንን ታሪካዊ አሸናፊነት የምንደግመው መሆኑን ከታሪክ እንድትማር ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡>>ብላል።

በሌላ ዜና ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባን ኪሙን ለግብጹ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲና ለኢትዮጵያውያው ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልክ በመደወል ፣ አገራቱ ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል።