ነሀሴ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል ባለስልጣናት በሕዝብ ታገቱ በእገታው ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ወጣቶች በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ታሰሩ በአማራ ክልል የክልሉ ባለስልጣናትን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪዎች፣ የሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ ባለስልጣናትና ሌሎች የክብር እንግዶች ተሰርቶ ያልተጠናቀቀ መንገድ ተረክበዋል በማለት በአካባቢው ነዋሪዎች መታገታቸውን ሰንደቅ ዘገበ።
እገታውም በድርድርና ውይይት ከተፈታ በኋላ መንገድ ዘግተዋል የተባሉ 12 ወጣቶች በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤በሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ ከድልብ እስከ ሙጃ ከተማ በ150 ሚሊዮን ብር የሚሰራው 27 ኪ.ሜ የገጠር ጠጠር መንገድ ኤም ኬ ኤች በተባለ ተቋራጭ በሶስት አመት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ቃል ገብቶ ነበር።
ነገር ግን የመንገዱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ የክልሉ ባለስልጣናት በተገኙበት ሐምሌ 15 ቀን 2004 ዓ.ም የመንገድ ርክክብ መፈፀሙ ከአካባቢዋ ነዋሪዎች ተቃውሞ ተነስቷል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ ከሚሰራው 27 ኪ.ሜ ውስጥ ከደንሳ እስከ ሙጃ ከተማ 6 ኪ.ሜ እንዲሁም ከእምባጮ ወደ ድልብ በሚወስደው መስመር ፍሳሽ በተባለው ቦታ የሶስት ኪሎ ሜትር ሳይጠናቀቅ የክልሉ ባለስልጣናት ከኮንትራክተሩ መንገዱ መረከባቸው የሕዝብን ቁጣ ቀስቅሷል።
በርክክቡም ወቅት የአካባቢዋ ነዋሪዎች ‘‘ያላለቀ መንገድ እንዴት ትረከባላችሁ? ከአፄ ኃይለስላሴ ስርዓት አንስቶ እስካሁን መንገድ ተሰርቶልን አያውቅም። መንገዱ በሙሉ ተጠናቆ ያልቃል ብለን ስንጠብቅ እንዴት ሳይጠናቀቅ ትረከባላችሁ?’’ በማለት የባለስልጣናቱን መኪና በማስቆም ‘‘አናግሩን’’ ይሏቸዋል። ባለስልጣናቱ ግን ‘‘አስቸኳይ ስራ አለብን’’ በማለት ነዋሪዎቹን ለማናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነዋሪዎቹ ‘‘አናሳልፍም’’ ይሉዋቸዋል።
በዚህ መሀል ከባለስልጣናቱ አንዱ ወደ ክልሉ ስልክ በመደወል፦ ‘‘በነዋሪው ስለታገትን በሄሊኮፕተር ፖሊስ ይላክልን’’ ሲሉ መልዕክት ለማስተላለፍ መገደዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በመጨረሻም የወረዳው የፖሊስ አዛዥ ተጠርተው ከመጡ በኋላ ውይይት እንዲካሄድ በመወሰኑ ህዝቡና ባለመስልጣናቱ ውይይት መጀመራቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ ያላለቀመንገድ የተረከቡት መንገዱ ደረጃ በደረጃ ስለሚሰራ እንደሆነ ባለስልጣናቱ ለህዝቡ ገለፃ መስተታቸውን አመልክተዋል።
ይሁንና የባስልጣናቱ መልስ ያልተዋጠላቸው የአካባቢው ወጣቶች፤ የባለስልጣናቱ ተሽከርካሪዎች የሚያልፉበትን መንገድ በመዝጋት ተቃውሞአቸውን በመቀጠላቸው 12 ወጣቶች ሊታሰሩ ችሏል።
ወጣቶቹም ከታሰሩ በኋላ የወረዳው ፍርድ ቤት በ400 ብር ዋስ ቢለቃቸውም፤ የዞን አስተዳደር ግን ወጣቶቹ ‘‘አሸባሪ ናቸው’’ በማለት እንደገና እንዲታሰሩ መደረጋቸውን ከ አካባቢው ነዋሪዎች ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ታሰሩ የተባሉት ወጣቶች አበበ በላይ፣ መሰለ አለሙ፣ ታምሩ ሽፈራሁ፣ ፋሲካው ኃየሎም፣ ኪዳኔ አድማሱ፣ ወንዲፍራው ካሳ፣ ደጀን ፈንታነው፣ እንዳልካቸው መዝሙር፣ መንበር ጌጤ፣ ሲሳይ ገበየሁ፣ በላይ በሁሉ፣ አሰፋ ድንበሩ፣ የሚባሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በወልዲያ ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን የግዳን ወረዳ አስተዳደር አቶ ደሳለ ሙሉጌታ ስለሁኔታው ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው ችግሩ ማጋጠሙን አምነው የታሰሩት አካላት ከመንገዱ ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ አድማና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ በመደረጉ ያንን ለመከላከል ሲባል እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ መብታችን ተጥሷል ብለው የተቃውሞ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎች ሁሉ የሽብርተኝነት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ይታወቃል።
____________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide