ወቅታዊው የዋጋ ግሸበት በ20 በመቶ አሻቀበ

ነሀሴ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም  የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ
አጠቃላይ የዋጋ ግሸበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ32 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን፣ወቅታዊው የዋጋ
ግሸበት ሁኔታ በተመሳሳይ መልኩ ከአምና ሐምሌ ወር ጋር ሲነጻጸር በ20 በመቶ ከፍ ማለቱን  ይፋ አደረገ፡፡

ኤጀንሲው ከትላንት በሰቲያ ይፋ ባደረገው ወርሃዊ ሪፖርቱ እንደገለጸው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ
ግሸበት ረዘም ያለጊዜን የዋጋ ግሸበትን ሁኔታን እንደሚያሳይ፣ካለፈው ኣመት ተመሳሳይ ወር ጋር ተነጻጽሮ የሚገኘው
ውጤት ወቅታዊውን የዋጋ ግሸበት ሁኔታ እንደሚገልጽ በሪፖርቱ አስረድቶአል፡

ለዚህ ጭማሪ ምክንያቱ በሀምሌ ወር 2004 ዓ.ም የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ 306 በመቶ ፣በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም
የተመዘገበው 254 ነጥብ 9 በመቶ አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ በልጦ በመገኘቱ ነው፡፡

በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም የአገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ  ከሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ጠቅላላ
ኢንዴክስ ጋር ሲነጻጸር በ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ይህው ሪፖርት በከፍተኛ ደረጃ ከናሩት ሸቀጦች
መካከል ልብስና ጫማ በ31 ነጥብ 5 በመቶ፣መጠጥ በ22 ነጥብ 8 በመቶ፣የቤት ዕቃዎች፣ቤት ማስጌጫዎች፣የቤት
ቁሳቁስና የቤት ሠራተኞች ደመወዝ በ25 ነጥብ 8 በመቶ፣ምግብ በ20 ነጥብ 8 በመቶ በመሆን በቅደም ተከተል
ከፍተኛውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

በተጨማሪም ሲጋራና ትምባሆ በ1 ነጥብ 7 በመቶ፣የቤት መሥሪያ ዕቃዎች ፣ውሃና ኢነርጂ
በ13 ነጥብ 7 በመቶ፣መዝናኛና ትምህርት በ15 ነጥብ 2 በመቶ፣የግል ንጽህና የግል ቋሚ ዕቃዎች በ19 ነጥብ 3
በመቶ እና ሌሎች ዕቃዎች በ19 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የምግብ ክፍሎች ካለፈው ዓመት ወር ጋር ሲነጻጸሩ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡በዚሁ መሰረት እህል በ25 ነጥብ
6 በመቶ፣ጥራጥሬ በ11 ነጥብ 7 በመቶ ዳቦና ሌሎች የተዘጋጁ ምግቦች በ20 በመቶ፣ሥጋ በ54 ነጥብ 8
በመቶ፣ወተት ዓይብና ዕንቁላል በ27 ነጥብ 9 በመቶ፣ድንች ሌሎች ሥራሥሮች በ43 ነጥብ 1 በመቶ፣ሌሎች ምግቦች
በ16 ነጥብ 4 በመቶ፣የማሰፈጫ አገልግሎት በ16 ነጥብ 3 በመቶ አሻቅበዋል፡፡

በተጨማሪም ከቤት ውጪ የተወሰዱ ምግቦች በየኢንዴክሶቻቸው በ28 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት አሳይተዋል፡፡
የኤጀንሲው መረጃ አይይዞም ትርንስፖርትና መገናኛ በ1 ነጥብ 3 በመቶ፣ዘይትና ቅባቶች በ10 ነጥብ 9
በመቶ፣ቅመማቅመም በ8 ነጥብ 8 በመቶ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር ቅናሸ ማሳየቱን ጠቅሷል፡፡

አገር አቀፍ የሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም የችርቻሮ ዋጋ ኢንዴክስ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  በ20
በመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ ምክንያት ከሆኑት ክልሎች መካከል ሐረሪ በ26 ነጥብ 1 በመቶ፣ትግራይ በ24 ነጥብ 5
በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ በ22 በመቶ፣ አፋር በ21 ነጥብ 4 በመቶ በቅደም ተከተል ከፍተኛውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረው የዶላር እጥረት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየናረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጭ እንዳያወጣው ተሰግቷል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide