ከፍተኛ የፖሊስ አዛዦች ሙስሊሙ ማህበረሰብ ህገመንግስቱን ለመናድ ከሞከረ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ሲሉ አስጠነቀቁ

ነሀሴ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የጀመሩት ተቃውሞ አንድ አመት ሊመላው ጥቂት ወራቶች ብቻ በቀሩበት በዚህ ጊዜ፣ የፖሊስ አዛዦች ተቃውሞው የሚቀጥል ከሆነ የከፋ ጉዳት ይከተላል ብለዋል።

የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ወርቅነህ ገበየሁ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፖሊስ ፕሮግራም ላይ ቀርበው እንደተናገሩት  ፣  ሙስሊሞች ፍላጎታቸውን በሀይል ለመጫን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ርብርብ የማይቆም ከሆነ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በፌደራል ፖሊስ በጸጥታ እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት የኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ፍጹም ግርማይ በበኩላቸው በህገ መንግስቱ ላይ የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ለመከላከል መስዋት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል::

መንግስት የሙስሊም እንቅስቃሴ መሪዎችን በማሰር ውዝግቡ ሊበርድ ይችላል ብሎ ተስፋ ቢያደርግም፣ ሙስሊሞች ግን መሪዎቻችን ይፈቱ የሚል ተጨማሪ ጥያቄ በማቅረብ  ትግላቸውን ከመቀጠል ውጭ ወደ ሁዋላ ለመመለስ ዝግጁ አለመሆናቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ሙስሊሞች መግለጻቸው ይታወሳለ።

በፖሊስ የቀረበው ማስጠንቀቂያ የሙስሊሙ እንቅስቃሴ መንግስትን በእጅጉ እያሰጋው መምጣቱን እንደሚያሳይ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ሙስሊም ገልጠዋል።

ሙስሊሙ የጠየቀው ጥያቄ ህገመንግስቱ ይከበርልን የሚል ሆኖ እያለ ፣ የፖሊስ አዛዞች ህገመንግስቱን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን ብለው መዛታቸው በመንግስትና በሙስሊሙ መካከል ያለው ውዝግብ በቀላሉ ሊበርድ እንደማይችል አመላካች ነው በማለት አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።

ከ500 ሺ በላይ የሚሆኑ ሙስሊሞች ባለፈው አርብ ነጭ ጨርቅ በመያዝ ተቃውዋቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፤ የፊታችን አርብም ተመሳሳይ ተቃውሞ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሎአል።

_____________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide