(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2011)በአለም እጅግ ከፍተኛ በሚል ድህነት ውስጥ ካሉ ዜጎች ግማሽ የሚሆኑት የሚኖሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት ሃገራት መሆኑ ተገለጸ።
እንደጥናቱ ቢሊየን ከሚበልጠው የዓለም ህዝብ 736 ሚሊየኑ በተጎሳቆለ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ መሆኑ ታውቋል።
ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሹ ማለትም 368 ሚሊየኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት የአፍሪካ ሃገራት የሚገኙ ናቸው።
የአለም ባንክ ባላፈው ቅዳሜ ይፋ ባደረገውና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 በተደረገው ጥናት መሰረት በዓለማችን ከፍተኛ የድሃ ቁጥር የያዙ ሃገራት በሚል የተዘረዘሩት 5 ሃገራት ሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሁም ባንግላዴሽና ኢትዮጵያ ናቸው።
እነዚህ 5 ሃገራት በ2015 ከተመዘገቡ 736 ሚሊዮን መናጢ ድሃዎች 368 ሚሊየኑን ይዘዋል።
የዓለማችንን ከፍተኛ የድሃ ቁጥር የያዙት 5 ሃገራት በደቡብ ኢስያና ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ክፍለ ዓለማት ያሉት አጠቃላይ የተጎሳቆሉ ድሆች በጠቅላላ 629 ሚሊየን መሆናቸውም ተመልክቷል።
በአለም ባንክ መመዘኛ ከፍተኛ ድሃ በሚል የሚጠቀሱት የቀን ገቢያቸው በአሜሪካ ዶላር ከ1 ብር ከ90 ሳንቲም ያነሰ የሚያገኙት ናቸው።
ይህም በኢትዮጵያ 54 ብር ማለት ነው።
ሕንድ 1 ቢሊየን 3 መቶ ሚሊየን ከሚሆነው ህዝቧ በፍጹም ድህነት የሚኖረው 13.4 በመቶ ብቻ ቢሆንም በህዝብ ቁጥሯ ትልቅነት ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።
ያም ሆኖ ግን ህንድና ባንግላዴሽ ከ10 ዓመት በኋላ ዜጎቻቸውን ከፍጹም ድህነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያወጡና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ፍጹም ደሃ የሌለባቸው ሃገራት እንደሚሆኑ ባለሙያዎች ተንብየዋል።
በኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ግን ድህነቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ነው ጥናቱ ያመለከተው።
ይህም የሃገራቱን እንቅስቃሴ መሰረት ባደረገ ጥናት ላይ የተመረኮዘ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።