የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በኢንዶኔዢያ ተገዶ እንዲያርፍ ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2011)የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የኢንዶኔዢያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ጥሷል በሚል በተዋጊ ጀቶች ተገዶ እንዲያርፍ መደረጉ ተገቢ ርምጃ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ገለጸ።

በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት የቺካጎ ኮንቬንሽን መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕገ-ወጥ ተግባር አለመፈጸሙን ገልጿል።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥር ET 32728 የሆነው የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላን ትናንት የኢንዶኔዥያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ጥሶ ገብቷል በሚል በሃገሪቱ የጦር ሃይል ጄት ተከቦ ባታም በተባለ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ መገደዱ ታወቋል።

አውሮፕላኑ በግድ እንዲያርፍ የተገደደው የኢንዶኔዥያን የአየር ክልል ያለፈቃድ በመግባቱ እንደሆነም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ላይ በማህበራዊ ገጹ በሰጠው ማብራሪያ የኢንዶኔዢያን የአየር ክልል ለማለፍ የሞከረው የቺካጎ ኮንቬንሽንን መሰረት በማድረግ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን-የጀት ሞተር ይዞ አስቀድሞ ያልታቀደ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ሲንጋፖር በማድረግ ላይ እያለ ችግሩ መከሰቱን አመልክቷል።

ወደ ሲንጋፖር በሚደረገው በረራ የኢንዶኔዥያን የአየር ክልል ያለቅድመ ፈቃድ ለማለፍ የተገደደው በረራው ድንገተኛ/ያልታቀደ ስለነበር እንደሆነም አመልክቷል።

ያልታቀደ በረራ በሚደረግበት ወቅት የወዳጅ ሃገር የአየር ክልልን ያለቅድመ ፈቃድ ማለፍ አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የቺካጎ ኮንቬንሽን አንቀጽ 5 ይፈቅዳል በማለት ርምጃውን ተቃውሟል።

ለጥገና የተጫነን ሞተር ይዞ ኢንዶኔዥያ ላይ የታገተው አውሮፕላን የበረራ ሰራተኞች በሆቴል ቆይታ ካደረጉ በኋላ ጉዞውን መቀጠሉንም ከአየር መንገድ መግለጫ መረዳት ተችሏል።