በናይጀሪያ ከ100 በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ሴት ተማሪዎች በታጠቁ ሀይሎች ከትምህርት ቤታቸው ተጠልፈው ተወሰዱ።

ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ እንደዘገበው  ታጣቂዎቹ  ሴት ተማሪዎቹን በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ ወደሚገኝ  ሩቅ ስፍራ ነው ይዘዋቸው የሄዱት።

የናይጀሪያ ወታደራዊ ሀይል  ክስተቱን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ  ከተጠለፉት 129 ታዳጊ ሴቶች ስምንቱ ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ አምልጠው መምጣታቸውን ቢገልጽም፤ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ግን አሁንም በርካታ ልጆች መጥፋታቸውን ነው እየተናገሩ ያሉት።

ድርጊቱን የፈፀመው “ቦኮ ሀራም” የተሰኘው እስላማዊ ቡድን መሆኑን የገለፁት የሀገሪቱ ባለሰልጣናት፤ቡድኑ የጠለፋቸውን ሴቶች በካሜሩን ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኝ ጫካ እንደወሰዳቸው አመልክተዋል።

ቦኮ ሀራም  በሰሜንቨ ናይጀሪያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ደም አፋሳሽ ውጊያ  ማወጁ ይታወቃል። ትናንት ረቡዕ በሰሜናዊ የ ሀገሪቱ ክፍል በሚገኘው በግዎዛ ቀጣና በሰነዘረው ጥቃት 18 ሰዎች ተገድለዋል።

በ አሁኑ ጊዜ  የ አገሪቱ አየር ሀይል፣ ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት የተጠለፉትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ የተቀናጀ ዘመቻ መጀመራቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባንኪ ሙን በሰጡት መግለጫ አስደንጋጩን የጅምላ ጠለፋ አጥብቀው በመኮነን፤ የተጠለፉት ሴት ተማሪዎች በ አስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።

በትምህርት ቤትና በተማሪዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ማነጣጠር ዓለማቀፉን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ መጣስ ነው” ብለዋል-ባንኪሙን -በመግለጫቸው።”