መጋቢት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታዋቂው የሰብኢ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ እንደገለጸው የናይጀሪያ መከላከያ ሰራዊት፣ የእስልምና መንግስት ለማቋቋም የሚታገለውን ቦኮ ሃራም የተባለውን ተዋጊ ሃይል ለመውጋት በሚል ሰበብ በከፈተው ጥቃት ከ600 በላይ ዜጎች ተገድለዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በሚወስደው እርምጃ በአለማቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቅ እንደሚገባው የገለጸው አምነስቲ፣ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎችም በተመሳሳይ ንጹሃን ላይ የሚወስዱት እርምጃ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል ብሎአል።
የናይጀሪያ መንግስት ለአምነስቲ ሪፖርት መልስ አልሰጠም።
ቦካ ሃራም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በናይጀሪያ ወታዳራዊ ካምፖች እና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛል። በቦኮ ሃራምና በመንግስት መካከል በሚደረገው ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አደጋ አንዣብቦባቸዋል። እስካሁን ደረስ ከ250 ሺ በላይ ናይጀሪያውያን ጦርነቱን በመስጋት ቀያቸውን በመልቀቅ ተሰደዋል።