የኩረጃ መስፋፋት የትምህርት ጥራትን እየጎዳ ነው ተባለ

መጋቢት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የብሔራዊ ፈተናዎች በተለይ የ8ኛ እና የ12 ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናዎች ላይ ኩረጃ በአሳሳቢ ደረጃ እየተባባሰ መምጣቱን፣ ለትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል አንድ ምክንያት እየሆነ መሆኑን የፌዴራል የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮምሽን ያካሄደው ጥናት ጠቁሟል፡፡

ሰሞኑን ይፋ ሆነው ይህው ጥናት በኩረጃው ሒደት በተቀነባበረ መልኩ ሁሉም አካላት ማለትም ፈተና
አስተባባሪዎች፣ፈታኞች፣ የፈተና ጣቢያ ሃላፊዎች፣ርዕሰመምህራን፣ መምህራን፣ ወላጆች በቀጥታ ይሳተፋሉ፡፡ እነዚህ አካላት የመልስ ወረቀቶችን አባዝቶ በመስጠት፣ መልሶችን በመስራት፣ ተማሪዎች ሲኮራረጁ ችላ በማለት፣ ወላጆች ደግሞ የሚመለከታቸውን ወገኖች በጥቅም በመደለል፣ ወደፈተና ጣቢያ የሚመጡ ፈታኞችን ደግሰው በመቀበል ተጽዕኖ እንደሚደርጉ ጥናቱ አመልክቶአል፡፡

ተማሪዎች በበኩላቸው ፈተናውን በጋራ የመስራት፣ፈተና ወረቀት ተለዋውጦ የመስራት፣ሁከት በመፍጠር ፈተናውን ማስተጉዋጎልና የመሳሰሉትን ያደርጋሉ ይላል፡፡

በዚህ መልኩ በኩረጃ የሚያልፉ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው፣ ቢገቡም ውጤታቸው ደካማ እንደሚሆን የተመለከተ ሲሆን ይህ ጉዳይ ለትምህርት ጥራት መውደቅ አንድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብሎአል፡፡

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በዓመት ለፈተና አስተዳደር እና ለፈተና ሕትመት 121 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ሲሆን የኩረጃ መስፋፋት ግን የዚህን ወጪ አስፈላጊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ጥሎታል፡፡ በኢትዮጵያ  የትምህርት ጥራት ከመቸውም ጊዜ በላይ መውደቁን የተለያዩ ምሁራን ይገልጻሉ።