በጉጂ እና በቦረና ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት የማቾች ቁጥር መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ

መጋቢት ፲፰ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት ባለፉት 3 ቀናት ከቦረና እና ከጉጂ ጎሳዎች ከ20 ያላነሱ ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ብዙ ቤቶች መቃጠላቸውንና መጠኑ በውል ያልታወቀ ንብረት መውደሙንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

በተለይ ትናንት ብቻ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በተነሳው ግጭት ከቦረና ከ12 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከጉጂ ደግሞ 8 ሰዎች ተገድለዋል። ኬንያ ውስጥ የሚኖሩ ቦረናዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ለመደገፍ በሚል መነቀሳቀሳቸው እየተሰማ ሲሆን፣ ፖሊስ አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ሊከሰት እንደሚችል ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በትናንትናው እለት የተወሰኑ የክልልና የፌደራል ፖሊሶች ወደ አካባቢው የተሰማሩ ሲሆን ፣ የፌደራል ፖሊሶች የሚጋጩትን ሁለቱን ሃይሎች ለመለያየት ሲሞክሩ ከጉጂ ጎሳ አባላት ጋር የተኩስ ለውጥጥ አድርገው እንደነበር ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ገልጸዋል። ከፖሊስ ወገን ምን ያክል እንደተጎዳ ለማወቅ ባይቻልም፣ ከጉጂ በኩል 6 ሰዎች በፖሊሶች መገደላቸው ታውቋል።

አልጌ፣ አዳዲ ቦኮ እንዲሁም ደካ ቀላ በሚባሉት ቀበሌዎች ውጥረቱ አሁንም ከፍተኛ ሲሆን፣ በተለይ በአልጌና ሰአንሰር አካባቢ መልካ ጉባ ወንዝን ይዞ ግጭቱ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ሙጋዩ፣ እና አዳዲ ቀበሌዎች ሁለቱም ጎሳዎች ተፋጠው ይገኛሉ።

ግጭቱ ከነገሌ ቦረና ስያሜ ጋር ተያይዞ ቢነሳም፣ የጉጅና የቦረና 2 ሹሞች ከስልጣን መውረዳቸው ግጭቱን እንዳባባሰው የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ነዋሪዎች መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ባለመውሰዱ የብዙ ሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ ።

የአካባቢው ሰዎች የወረዳውን ባለስልጣናት እና የፌደራል ስርአቱን አወቃቀር ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሁለቱም ጎሳዎች ለዘመናት ተቻችለው የኖሩ መሆናቸውና ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህ ግን እየተጋጩ መምጣታቸውን ይናገራሉ።