ግንቦት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሰሜን ጎንደር የታች አርማጭሆ ሰብሳቢ የሆኑት ሚያዚያ 17 ፣ 2005 ዓም በቁጥጥር ስር በዋሉበት እለት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ቤተሰባቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
እህታቸው ወ/ሮ የንጉሴ ሲሳይ ወንድማቸው ተዘቅዝቆ ለረጅም ሰአታት እንዲቆይ መደረጉን፣ በእጆቹ ጣቶች መካከል ብረት እንዲገባ በመደረጉ ጣቶቹ ሽባ መሆናቸውን እንዲሁም እግሮቹ በድበዳ መመለጣቸውን እያለቀሱ ተናግረዋል። አቶ ተገኝ በድብደባ ብዛት ለመሞት ሲቃረቡ ፖሊሶቹ በድንገት ሆስፒታል እንደተወሰዱ የገለጹት ወ/ሮ የንጉሴ፣ ግንቦት21 ቀን የነበራቸው ቀጠሮም ወንድማቸው ለመዳን ባለመቻሉ ሳይቀርብ መቅረቱን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የፖሊስ ጣቢያውን አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ወረታው አለምን ያነጋገርናቸው ሲሆን፣ ኢንስፔክተሩም በሰጡት ምላሽ አቶ ንጉሴ አለመደብደባቸውን መታችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ፣ ከዚህ በስተቀር ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት አልችልም ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአንድነት ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሙላት ፍሰሀ አቶ ተገኝ ከሌሎች 8 ሰዎች ጋር በትጥቅ ትግል መንግስትን ለማስወገድ ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ቢያዝም ፣ ድርጅታቸው የሚያውቀው በአንድነት ፓርቲ አመራርነቱ ነው ብለዋል።
በዚሁ ዞን በቃሮራ ወረዳ በሶረቃ ከተማ በተመሳሳይ መንገድ 7 ሰዎች ተይዘው ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ለማወቅ ተችሎአል።