የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሊኒየሙ የልማት ግብ ሲጠናቀቅ በህገወጥ የገንዝብ ዝውውር ላይ እንደሚዘምት አስታወቀ

ግንቦት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አለማቀፍ እውቅና ያላቸውን ሰዎች ያካተተው የተመድ ከፍተኛ ፓናል ፣ የሚሊኒየም የልማት ግቦች መርሀግብር ከሁለት አመት በሁዋላ ሲጠናቀቀር ፣ በህገወጥ መንገድ ከደሀ አገሮች እየተዘረፈ በውጭ ባንኮች  በሚቀመጠው ገንዘብ ላይ ፊቱን እንደሚያዞር  አስታውቋል።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ከላከው ዜና ለመረዳት እንደተቻለው ፣ በአለፉት 30 አመታት ከአፍሪካ 1 ትሪሊዮን 300 ቢሊዮን ዶላር ተዘርፎ በውጭ ባንኮች ተቀምጧል።

የግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ፕሬዚዳንት ራይሞንድ ባከር  ” ዜናው ለደሀ አገሮች  ብስራት ይዞ የመጣ ነው” ብለውታል።  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋናውን የድህነት መንስኤ ለመጋፈጥ ትክክለኛ እርምጃ ወስዷል ሲሉም አወድሰዋል።

ኢትዮጵያ ገንዘብ በህገወጥ መንገድ እየተዘረፈ ወደ ውጭ ባንኮች ከሚላክባቸው ቀዳሚ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ ባለፉት 9 አመታት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ ወደ ውጭ ባንኮች ተላልፎአል።