በባህርዳር ከ17 ሰዎች ሞት ጋር በተያያዘ ከታሰሩት 22 ፖሊሶች መካከል 4ቱ ተፈቱ

ግንቦት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቅርቡ በባህርዳር ከተማ 17 ንጹሀን ዜጎችን በግፍ ከገደለው የፌደራል ፖሊስ አባሉ ፈቃዱ ናሻ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል 4ቱ ዛሬ ሲለቀቁ፣ 5ቱ ደግሞ ከስራ ተባረዋል።

ከዚህ ሌላ  2ቱ ፖሊሶች በከፍተኛ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ሲደረግ፣ 9ኙ ደግሞ በህዳር 11 ፖሊስ ጣቢያ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።

ሥለ ጉዲዩ  ምስክርነት የሰጠችው የፖሊስ መኮንኗ ” በእለቱ በሌላ አካባቢ ወንጀል በመፈጸሙ  አራቱን ፖሊሶች ወደ ሌላ ቦታ ልኬያቸዋለሁ” የሚል ቃል በመናገሩዋ፣ ፖሊሶቹ ለመለቀቅ እንደቻሉ ታውቋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት በቂ ሆነ የእርምት እርምጃ አልወሰደም በሚል ተቃውሞአቸውን  እየገለጹ ነው ። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ተቃውሞ ለማሰማት የሞከሩት ነዋሪዎች በፖሊስ ጣልቃ ገብነት የተነሳ ሳይሳካላቸው መቅረቱ ይታወሳል።