ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ ከመቀሌ በላከው ዘገባ እንዳመለከተው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የክልሉ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ የአቶ መለስ ዜናዊ ህመም ነው። ሁለት አይነት አስተያየቶች ይቀርባሉ የሚለው ዘጋቢያችን፣ አንደኛው ወገን አቶ መለስ አርፈዋል ብሎ የሚያምን ሲሆን ሌላኛው ወገን ግን ህመማቸው ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ብሎ ያምናል።
የአቶ መለስን ህመም ተከትሎ በክልሉ ይህ ነው የሚባል የተለየ እንቅስቃሴ እንደሌለ የጠቀሰው ዘጋቢያችን፣ ይሁን እንጅ ጉዳዩ የህዝቡን ትኩረት መሳቡንና በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ ስለመጪው ጊዜ ውይይት መጀመሩን ገልጧል።
በክልሉ የሚኖሩ አንድ የህወሀት መስራችና አሁን የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባል ” የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ዛሬ ቢደበቅም፣ ነገ ይፋ መሆኑ አይቀርም። በአንድ ሰው ላይ ይህን ያክል ወሬ መወራት ከጀመረ ለሰውየውም ጥሩ አይደለም።” በማለት ለዘጋቢያችን ተናግረዋል። የአቶ መለስ ህመም በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ የማያመጣ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
የአቶ መለስ ህመም በመላ አገሪቱ የህዝቡን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ በርካታ በአገር ቤት እና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በመደወል ” የአቶ መለስ ጉዳይ ምን ደረጃ ደረሰ በማለት እየጠየቁ ነው።” ኢሳት አቶ መለስ ተኝተውበታል በተባለው ሆስፒታል ሁሉ በመጠያየቅ መረጃ ለማሰባሰብ ሙከራ ቢያደርግም ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት እስካሁን አልተሳካለትም።
ዛሬ የፍትህ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ በፌስ ቡክ ላይ አቶ መለስ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ዘገቧል።
ተመስገን ደሳለኝ እንደዘገበው፤ መለስ ድነው ይሁን አለያም “ከዚህ በሁዋላ አትድንም ተብለው በህክምና ተስፋ ቆርጠው” ባይረጋገጥም፤ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ መግባታቸው ተረጋግጧል።
የ አቶ መለስን መታመም ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ አራት ቡድኖች ተፈጥረው የስልጣን ግብግብ እንደገጠሙም ተመስገን ዘግቧል።
የአቶ መለስ ህመም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ትኩረት በመሳቡም፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ አምባሳደሮች ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርበዋል። መንግስት የአቶ መለስ ህመም ለጉዳት የማይዳርግ መሆኑን ለዲፕሎማቲክ ምንጮች መግለጹ ታውቋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide