የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2005 በጀት እያነጋገረ ነው

ሐምሌ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2005 በጀት ዓመት ለአስሩ ክፍለ ከተሞች በድምሩ 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በዓላማ ላልተገደበ ተግባር ማወሉ እያነጋገረ ነው፡፡

የአቶ ኩማ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ለ2005 በጀት ያጸደቀው 16 ቢሊየን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ክፍለከተሞች እንደፈለጉት ሊመነዝሩት የሚችሉት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ባልተለመደና ከበጀት አያያዝና አጸዳደቅ ፍጹም በተለየ መልኩ እንዲመደብላቸው አድርጓል፡፡
ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይህ ልዩ በጀት በ2005 ዓ.ም በሚካሄደው የአዲስአበባ ከተማ ምርጫ ገዥው ፓርቲ እንዳሻው የሚጠቀምበት ነው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እነዚሁ አሰተያየት ሰጪዎች አያይዘውም ዓመታዊ በጀት መስሪያቤቶች ሲያቀርቡ እያንዳንዱን ወጪ በዝርዝር አቅርበውና እሱም ካለው በጀት ጋር ታይቶና ተገምግሞ
የሚፈቀድበት የተለመደ አሰራር መኖሩን ጠቅሰው በዚህ መንገድ ክፍለከተሞቹ ለ2005 በጀት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደተመደበላቸው ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ክፍለከተሞቹ ያልጠየቁትና በዓላማም ሳይገደብ ለፈለጉት
ተግባር የሚውል ከፍተኛ በጀት የተያዘበት አግባብ እንቆቅልሸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፓርላማ በ2005 በጀት ዓመት ለምርጫ ቦርድ 19 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ያጸደቀ ሲሆን ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 13 ነጥብ 7 ሚሊየን ብሩ ቦርዱ ለክልል አስተዳደሮችና የአካባቢ ምርጫ የሚያውለው ነው፡፡

ይህ ገንዘብ የአዲስአበባ አስተዳደር ለክፍለከተሞቹ እንደፈለጉ እንዲጠቀሙበት ከመደበው በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫ በቀጣይ የኢትዮጽያዊያን 2005 ዓ.ም እጅግ ቢዘገይ እስከ ግንቦት ወር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide