በትናንትናው እለት በአንዋር መስጊድ ሙስሊሞች ተቃውሞአቸውን አሰሙ

ሚያዚያ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እጅግ በርካታ ህዝብ በተገኘበት በዚሁ ስነስርአት ላይ ሙስሊሞቹ የአላህን ታላቅነት ሲያውጁ፣ መንግስት የአህባሽን አስተምህሮ ለማስፋፋት እና የመጅሊስ አመራሮችን  ለመሾም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አውግዘዋል። ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሙስሊሞች እንዳሉት መንግስት ለራሱ የሚመቹትን የመጅሊስ አመራሮች ለመሾም እየተንቀሳቀሰ መገኘቱ አበሳጭቶዋቸዋል።

ዳውድ ይባላል፣  የ20 አመት ወጣት ነው። መንግስት ሙስሊሞች  ላቀረቡት የመብት ጥያቄ ቀጥተኛ የሆነ መልስ ከመስጠት ጥያቄውን ለማድበስበስ መሞከሩን ይቃወማል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ መብቱን ለማስጠበቅ ዝግጁ ቢሆንም፣ መሪዎቹ የህዝቡን ጥያቄ ይዘው እሰከምን ደረጃ ሊገፉ እንደሚችሉ ግን እንደማያውቅ ገልጧል። ሩቂያ ደግሞ የአወልያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን፣ ዘወትር አርብ እየተገኘች የሙስሊሙን ችግር ለማሰማት በመቻሉዋ ደስተኛ ነች። በእርሷ አቋም ቤተሰቦቹዋ ደስተና መሆናቸውንም ተናግራለች።

የኢሳት ዘጋቢ እንደገለጠው ሙስሊሞቹ ጥያቄያቸውን ለመንግስት ባለስልጣናት አቅርበው መልስ ከመጠበቅ ውጭ፣ ሌሎች የትግል አማራጮችን ለመጠቀም የመሪዎቻቸውን ፈቃድ ይጠይቃሉ። ብዙ ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ፍላጎት ቢናራቸውም፣ መሪዎቹ ግን ትግሉን በተራዘመ እና በሰከነ መንገድ ለመምራት የፈለጉ ይመስላል፣ ይህም ስትራቴጂ በተወሰነ መጠን የተሳካላቸው ይመስላል፣ ቀስ በቀስም መላውን ሙስሊም ከጎናቸው ለማሰለፍ ከመቻላቸውም በላይ  በሚሰጡት በሳል አመራር መንግስትን ግራ አጋብተውታል በማለት ገልጧል። መንግስት በአወሊያ እንዳይሰባሰቡ ሲያግዳቸው ፣ መሰባሰቡን በእየመስጊዱ አደረጉት፣ ድሮ በአንድ ቦታ የነበረው ተቃውሞ አሁን በመላ አገሪቱ ተሰራጨ፣ በየአገሩ የሚታየው ዳግም አወልያ ነው ሲል የተመለከተውን ዘግቧል። በሙስሊሙ ወገን ያለው ስሜት ከሳምንት ሳምንት እየጠነከረ መምጣቱን መንግስትን በእጅጉ እንዳስፈራውም አልሸሸገም። መንግስት ሙስሊሙን ለማስፈራራት የተወሰኑ ሙስሊሞችን በቴሌቪዥን አቅርቦ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው አሸባሪዎች ናቸው ብሎአል፣ ሙስሊሙ ግን ለመንግስት ማስፈራሪያ ቁብ እንዳልሰጠ በየመስጊዱ ከሚታየው የህዝብ ስሜት በቀላሉ ለማየት ይቻላል ሲል ዘገባውን አጠቃሏል።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide