በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የትንሳኤን በአል በማስመልከት ቃለ ቡራኬ ሰጠ

ሚያዚያ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የህጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቅዱስ ሲኖዶስ በሚል መግለጫው የትንሳኤን በአል በማስመልከት ቃለ ቡራኬ ሰጠ

ሲኖዶሱ ለኢሳት በላከው ቃለ ቡራኬ የትንሳኤ በአል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከምታከብራቸው አበይት የጌታ በአላት በታላቅነቱና በክብሩ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ በአል መሆኑን አስታውሶ ፣ በትንሳኤው የክርስቲአኖች ህይወት ዋስትና ታውጇል፣ ሀሰተኞች የደረደሩት የሀሰት ክስ በሙሉ ተደምስሶ ሞትም ተሸንፎ የሞት አስፈሪነት ሳይቀር ጠፍቷል ብሎአል።

ሲኖዶስ በቃለ ቡራኪው ” አሁን ባለንበት ዘመን እንደ ጥንቱ ሁሉ ብዙ መዋእለ ንዋይ እውነትን ለመቅበር ይፈሳል፣ አሁን ይህን የነጻነት በአል እያከበርን ብዙ ንጹሀን ወገኖቻችን በእስር ቤት ታጉረዋል፣ ብዙ ህጻናት የሚበሉት አጥተው በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ ነው፣ ብዙ አባዎራዎች ለመለመን አፍረው የትንሳኤን በአል ማክበር አቅቷቸው በስቃይ ላይ ናቸው፣ በሀገራችን የመኖር መብታቸውን ያጡ በደቡብ የነበሩት ወገኖቻችን የሚያርሱትን መሬታቸውን ፣ ያፈሩትን ንብረታቸውን ተቀምተው በሀገራችን ላይ ተሰደው ትንሳኤን በሀዘን እያሳለፉት ነው ። በማለት ገልጧል።

በእና ዘመን የክርስቶስን ሞትና ትንሳኤ እየመሰከሩ ለሀገራችን እየጸለዩ የሚኖሩ መናንያን ትንሳኤውን በሀዘን እንዲያሳልፉት በመደረጉ ቤተክርስቲያኑዋ ማዘኑዋን ገልጦል።

በታሪክ ውስጥ የአለም መሪዎች ክርስትናን ለማጥፋት ያላደረጉት ጥረት የለም የሚለው መግለጫው፣ አሁን የእኛዎቹ እንደሚያደርጉት ሁሉ ክርስቲአኖች መገደላቸውን፣ በእሳት መቃጠላቸውን አስታውሶ ፣ እነዚያ አምባገነኖች ዛሬ የለሉ መሆናቸውን ቅዱሳን ግን ለዘላለም በህይወት ዋስትና በሆነው ትንሳኤ ተጠብቀው ይኖራሉ ብሎአል።

በመከራና በእስር ላይ ያሉ ሁሉ መከራው ያማያልፍ አይመስላቸውም ይሆናል ነገር ግን የትንሳኤ ጌታ በህይወት እያሉ ነጻነታቸውን አጥተው ከህዝባቸው ከቤተሰባቸው ተለይተው ፣ በእስር ቤት በስደት የሚገኙትን ወገኖቻችንን ሁሉ ከተጣሉበት እስር ቤት ከደረሰባቸው ፈተና ከክፉ የአገዛዝ ቀንበር ነጻ እንደሚያወታቸው ቃለ ቡራጌው አመልክቷል።

ቡራኬው በመጨረሻም ለሀገራችን ሰላምን ለቤተክርስቲያኒቱም አንድነትን ተመኝቷል።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide