በባህርዳር ጊዮን ሆቴል ጉዳይ የተነሳ የአማራ ክልል ባለስልጣናትና ህወሀት ተፋጠዋል

 መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የዛሬ 21 አመት ህወሀት/ ኢህአዴግ አሸንፎ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት ለህወሀት በመሰለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው የሚታወቁት በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአድዋው ተወላጅ እና የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ዘመድ አቶ ወልዱ፣ ለህወሀት  ላበረከቱት አስተዋጽኦ ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የመንግስት ንብረት የሆነውን ጊዮን ሄቴልን በ5 ሺ ብር ኪራይ እንዲሰሩበት በገጸ በረከት ስጥተዋቸው ነበር።

አቶ ወልዱ በልጃቸው በአቶ ብስራት ወልዱ ዋና አስተዳዳሪነት ሆቴሉን ሲሰሩበት እና ከፍተኛ ግብር ሲያጋብሱበት ከቆዩ በሁዋላ፣ ህዝቡ በባህርዳር ከተማ አንድ ኪዎስክ በ5 ሺ ብር እየተከራየ ጊዮን ሆቴልን የሚያክል በስፋቱና በጥራቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ሆቴል እንዴት መንግስት በ5 ሺ ብር ያከራያል በማለት ተቃውሞ ሲያሰማ መቆየቱን ተከትሎ፣ የፌደራል የኪራይ ቤቶች ድርጅት የክልሉ መንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሆቴሉን እንዲረከብ ለአማራ ክልል ቤቶች አስተዳዳር አምና ደብዳቤ ጽፏል።

ሆቴሉን እንዲያስረክቡ ድብዳቤ የደረሳቸው አቶ ወልዱ  በቀጥታ ለአቶ በረከት ፣ ለፌዴሩሽን ምክር ቤት ሰብሳቢው ለአቶ ካሳ ተክለብርሀንና ለቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሰ ፣ የብሄር ብሄረሰቦችን በአል ለማክበር አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት፣ አቶ መለስ ዜናዊ መሞታቸውን ተክትሎ ቤቱን እንዲያስረክቡ መጠየቃቸውን በመናገራቸው፣ ባለስልጣኖቹ የክልሉ መንግስት የጻፈውን ደብዳቤ እንዲያነሳ መጠየቃቸው ታውቋል።

የክልሉ ቤቶች ኤጀንሲ ጉዳዩ ከፍተኛ ዝርፊያ መሆኑን ቢገልጽም፣ የሆቴሉ አስተዳዳሪ የአቶ ወልዱ ልጅ ብስራት ወልዱ የክልሉን ባለስልጣናት በማስፈራራት እርምጃ እንደሚወስድ በመዛት ሆቴሉን ለማስረከብ ፈቃደኛ እንደማይሆን በመግለጹ ክልሉ የሚያደርገው ጠፍቶት ተቀምጧል። የከተማው ህዝብ በበኩሉ የክልላችንን ባለስልጣኖች አንድ የህወሀት አባል ሰው እንደልቡ እያሽከረከራቸው  በማለት ትችት እያቀረበ ነው። ህዝቡ በተደጋጋሚ የሆቴሉን ጉዳይ አንድ እልባት እንዲሰጠው እየጠየቀ ቢሆንም፣ የክልሉ ባለስልጣናት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እያስታወቁ ነው።

የጊዎን ሆቴል በጣና ዳር የተሰራ በርካታ አልጋዎችን በቀን ከ175 እስከ 250 ብር በሚደርስ ዋጋ ለቱሪስቶች የሚያከራይ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ሆቴሉ ሲሄዱ በነጻ የሚስተናገዱበት፣ በውስጡ የያዘው ቡናና ፍራፍሬ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ዘመናዊ ሄቴል ነው። የድርጅቱ የቀን ገቢ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ቢሆንም ፣ ባለሀብቱ በወር የሚከፍሉት የኪራይ መጠን 5 ሺ ብር ብቻ ነው። ጭቅጭቅ ከተነሳበት ከአምና ጀምሮ ደግሞ ባለሀብቱ የአምስት ሺ ብር የቤት ኪራይ መክፈል ማቆማቸው ታውቋል።

ከምንም የተነሱት የሆቴሉ ባለቤት ከ21 አመታት በሁዋላ እጅግ የናጠጡ ሀብታም ለመሆንና የተለያዩ ድርጅቶችንም ለመክፈት ችለዋል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንለት አንድ የኪራይ ቤቶች ድርጅት ሰራተኛ ” ግለሰቡ ቤቱን እንዲያስረክቡ ሲጻፍላቸው ዋጋህን ታገኛለህ” የሚል መልስ መስጠታቸውን ገልጿል። የክልሉ መንግስት እየደረሰበት ካለው ትችት ነጻ መሆን የሚችለው ግለሰቡ ሆቴሉን እንዲያስረክቡ ሲያደርግ እና እንደማንኛውም ሰው ተጫርተው ተገቢውን ክፍያ መክፈል ሲችሉ ብቻ ነው” ብሎአል።

አንድ ሌላ የባህርዳር ነዋሪ ደግሞ  ጊዮን ሄቴል ህወሀት በክልላችን ያለውን የበላይነት ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ነው ብሎአል።

በጉዳዩ ዙሪያ የሆቴሉን ባለቤትም ሆነ የክልሉን መንግስት ለማግኘት ያደርገው መኩራ አልተሳካም። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የአንድ ዘር የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የበላይነት የአገሪቱ መነጋጋሪያ እየሆነ መምጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።