(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011)በባህርዳር የነዳጅ እጥረት ተከሰተ።
ከባህርዳር በተጨማሪ በዙሪያዋ ባሉ ከተሞችም በነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን በመጥፋቱ ህዝቡ ችግር ላይ መውደቁን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ላለፉት ሶስት ቀናት ማደያዎች ነዳጅ ማቅረብ ባለመቻላቸው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች በጥቁር ገበያ ከመደበኛው ዋጋ በእጥፍ እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
የነዳጅ እጥረቱን በተመለከተ በክልሉ መንግስት በኩል የተሰጠ ማብራሪያ ባለመኖሩ የችግሩን መንስዔ ለማወቅ እንዳልተቻለ ተመልክቷል።
በባህርዳር ከተማ ጨምሮ በዙሪያ ከተሞች ካለፉት 3 ቀናት ወዲህ በነዳጅ እጥረት ነዋሪው ምሬት ውስጥ ገብቷል።
በባህርዳር ከተማ በአብዛኛው ማደያዎች ቤንዚን የለም የተባለ ሲሆን በአንዳንድ በተገኘባቸው ማደያወች በርካታ ተሽከርካሪዎች በረጅም ሰልፍ እየተጠባበቁ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተለይም የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ረጅም ወረፉ ይዘው በመጠበቅ በርካታ ሰዓታትን ለመቆም ተገደዋል።
በፖፒረስ ሆቴል ስር ባለው ማደያ ቤንዚን የለም የሚል ፅሁፍ የተቀመጠ ሲሆን ለበርካታ ቀናት ዝግ ሁኖ መቆየቱ ተመልክቷል።
በአዴት መውጫ ጎርደማ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ባለው ማደያ ረዥም የተሽከርካሪዎች ሰልፍ መታየት ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።
በተለይም የባለ 3 እግር(ባጃጅ) ትራንስፖርት ሰጭዎች ሰልፍ በየነዳጅ ማደያው እንደሚታይ ነው ለማወቅ የተቻለው።
በባህርዳር ዩንቨርስቲ ይባብ ካምፕስ ቤንዚን አለ በመባሉ በርካታ ተሽከርካሪዎች ረዥም ወረፋ ይዘው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።
በዛሬው ዕለት ማደያዎችን ተዟዙሮ የተመለከተው የኢሳት ወኪል በባህርዳር ከተማ ውስጥ እና ከከተማ ውጭ ባሉ አብዛኛው ማደያወች ቤንዚን አለመኖሩን አረጋግጧል።
በባህርዳር ከተማ ውስጥ ባሉ ማደያወች ቤንዚን አለመኖር ጋር ተያይዞ ተሽከርካሪዎች ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው ለመቆም ተገደዋል።
የታክሲ አገልግሎት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል ብለዋል ነዋሪዎች።
እጥረቱ ለህገወጥ የቤንዚን ሽያጭ ገበያ የከፈተ መሆኑን የገለጸው ወኪላችን በጥቁር ገበያ በሊትር 25 ብር እየተሸጠ ነው ብሏል።
በጥቁር ገበያ ቤንዚን እየገዙ የሚጠቀሙ የትራንስፖር አሽከርካሪዎች ህበረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር ለችግር አጋልጠውት እንደሚገኙ ከወኪላችን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከባህርዳር ከተማ ሌላ በዙሪያው ከተሞችና በደቡብ ጎንደር ወረታ ቤንዚን አለመኖሩ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።
እጥረቱ የተከሰተበትን ምክንያት በተመለከተ በክልሉ መንግስት በኩል እስከአሁን የተሰጠ ማብራሪያ የለም።