የአቶ ጌታቸው አሰፋ ሃብት እንዲታገድና የዝውውር መብታቸው እንዲገደብ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011) የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሃብታቸው እንዲታገድና የዝውውር መብታቸው እንዲገደብ አንድ የአሜሪካ ኮንግረስ ማን ጠየቁ።

የኮሎራዶው ኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍ ማን የኤች አር 128 የውሳኔ ሀሳብን ጠቅሰው በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ለሁለት የአሜሪካ ሚኒስትሮች የጻፉትን ደብዳቤ ዛሬ አስገብተዋል።

ኮንግረስ ማን ኮፍ ማን አቶ ጌታቸው አሰፋ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡና በውጭ ያላቸው ሃብት እንዲታገድ መጠየቃቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ስማቸው ጎልቶ ይጠቀሳል። የኢትዮጵያውያን ስቃይና መከራ እንዲያበቃ የሚቻላቸውን እያደረጉ ከሚገኙ የአሜሪካን ፖለቲከኞች በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ ናቸው።

ከኮሎራዶ የህዝብ እንደራሴ በመሆን በአሜሪካን ምክር ቤት የሚገኙት ማይክ ኮፍ ማን የውሳኔ ሀሳብ ሆኖ የጸደቀው የኤች አር 128 ዋና ስፖንሰር መሆናቸውም ይታወቃል።

እኚህ የአሜሪካን ኮንግረስ ማን ዛሬ አንድ ደብዳቤ ለሁለት የአሜሪካን ሚኒስትሮች ማስገባታቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍማን የቀድሞ የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ በኤች አር 128 የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ያስገቡት ለአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ለሀገር ውስጥ ገቢ ሚኒስትር ነው።

በደብዳቤው እንደተመለከተው የቀድሞ የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በመጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሰው ልጅ ላይ በሚፈጽም ወንጀል የሚጠይቅ ግለሰብ ነው።

ከዘጠኙ የህወሀት ቁልፍ ሰዎች አንዱ እንደሆኑ የሚጠቅሰው ደብዳቤው በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸሙ በተለይም ዘር ተኮር ለሆኑ ፍጅቶች በዋናነት የሚፈለጉ ሰው ናቸው ይላል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ ይገኛሉ ያለው ደብዳቤው የህወሀት የደህንነት ቢሮ ሃልፊ ሆነው መሾማቸውንም ይጠቅሳል።

ይህ አደገኛ ግለሰብ በስልጣን ላይ መቆየቱ በኢትዮጵያውያን ላይ ተጨማሪ አደጋ ለመፍጠር እድሉን እንዲያገኝ ያደርገዋል በማለት ማይክ ኮፍ ማን በደብዳቤው ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

በመሆኑም ይላሉ ኮንግረስ ማን ማይክ፡ በግለሰቡ የተፈጸሙት ወንጀሎችን መነሻ በማድረግና በቀጣይም አደጋ የመፍጠር አቅም እንዳላቸው በማሳሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካን መንግስት የረቀቀው የማግኒትስኪ ህግ ተግባራዊ እንዲደረግ እጠይቃለሁ ብለዋል።

በዚህም መሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ በአቶ ጌታቸው አሰፋ የቪዛ ማዕቀብና የሀብት እገዳ እንዲያደርጉ አሳስባለሁ ያሉት ማይክ ኮፍማን አሜሪካ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሰብዓዊ መብት መከበር ላይ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ማሳይት አለባት ሲሉ አጽንኦት በምሰጠት አሳስበዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ በመውሰድ ማንም ሰው ወንጀል ሰርቶ እንደማያመልጥ አሜሪካ አቋሟን የምታሳይበት መሆን እንዳለበትም ማይክ ኮፍ ማን በደብዳቤቸው ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ ጋር ወዳጅ የሆኑ ሀገራትም በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የሚደረገውን የጉዞና ዝውውር ገደብ ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ኮንግረስ ማን ማይክ ያሳሰቡት።

ከኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍ ማን ጋር በጋራ የሚሰራው የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪል ካውንስል ለኢሳት እንደገለጸው በኢትዮጵያ መንግስት በኩልም አቶ ጌታቸው አሰፋን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ጋር አብረን ለመስራት የምንችልበትን መንገድ እያፈላለግን ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፉትን እንደነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ዓይነቱን ወንጀለኛ በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ድጋፍ እናድርግ ሲልም ካውንስሉ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ የክስ ማዘዣ መቁረጡን ኢሳት መዘገቡ የሚታወስ ነው።