የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011)       በውጭና በሃገር ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጀመሩ።

በየአመቱ በጥቅምትና በግንቦት ወር የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከ25 አመታት በላይ ለሁለት ተከፍሎ ሲካሄድ ቆይቷል።

ዛሬ ሰኞ የካቲት 12/2011 አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሃገራዊ ሁኔታ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከርም ኮሚሽን እንደሚቋቋም ተመልክቷል።

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለሁለት ተከፍላ የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ በወረደው እርቅ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ከ25 አመታት በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

በፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስና በፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በጋራ እየተመራ ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።