(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4/2010)በኢሉባቡር ቡኖ በደሌ ባለፈው ቅዳሜ 12 የአማራ ተወላጆች በፖሊስ ተደብድበው መታሰራቸው ተገለጸ።
በደዴሳ ወረዳ ሰቦ ቀበሌ የሚኖሩት የአማራ ተወላጆች ድብደባ የተፈጸመባቸው በማሳቸው ላይ ምርት እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት በቄለም ወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን በመጥቀስ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በቡኖ በደሌ የታሰሩት የአማራ ተወላጆች እንዲፈቱም በመጠየቅ ላይ ነው።
ቡኖ በደሌ ደዴሳ ወረዳ ሶቦ ቀበሌ። ቅዳሜ ዕለት የአማራ ተወላጅ የሆኑና በአካባቢው ዓመታትን ያስቆጠሩት ነዋሪዎች በማሳቸው ምርት እየሰበሰቡ ነበር።
እዚያው በማሳቸው እያሉ ፖሊስ ይመጣል። ከዚያ በኋላ የሆነው ድብደባ ብቻ ነበር።
ወደ ፖሊስ ጣቢያም ተወስደው ድብደባው መቀጠሉን ነው ከስፍራው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
12ቱ የአማራ ተወላጆች በፖሊስ ድብደባ የተፈጸመባቸው ምክንያት አልታወቀም።
ከመሃከላቸው አብዛኞቹ ከአንድ ሳምንት በፊትም ታስረው የተለቀቁ እንደሆነ ይነገራል።
ባለፈው ህዳር ላይ በቡኖ በደሌ የአማራ ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩት አካባቢውን ለቀው መሰደዳቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ችግሩን ለመፍታት ተችሏል በሚል የተፈናቀሉት ሲመለሱ እዚያው ቀርተው የነበሩትም የተረጋጋ ህይወት መቀጠላቸው ተገልጾ ነበር።
ከ6ወራት በኋላ በድጋሚ ጥቃት መጀመሩን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ቅዳሜ ስለታሰሩት የአማራ ተወላጆች ለመጠየቅ ወደ ደዴሳ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ስልክ ደውለን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ዛሬ ሶስተኛ ቀናቸውን በእስር ቤት ያስቆጠሩት የአማራ ተወላጆቹ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውም ታውቋል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በቄሌም ወለጋ ዞን ሲዮ ወረዳ በአካባቢው ወጣቶች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወጣቶቹ በአማራ ተወላጆች ንብረት ላይ የማውደምና የዘረፋ ተግባር መፈጸማቸውንም አምንስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ለሰብዓዊ መብቶች የሚቆረቆር ዓለም ዓቀፍ ድርጅት መግለጫ በማወጣት ገልጿል።
አምንስቲ እንዳለው በአማራ ተወላጆቹ ላይ ጥቃቱ ሲፈጸም የአካባቢው ፖሊሶችም ሆነ ባለስልጣናት ለማስቆም የወሰዱት እርምጃ አልነበረም።
እንደአምንስቲ መግለጫ ከ1400 በላይ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለዋል።
ካለፈው ህዳር ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ጥቃትም 20 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ነው በአምንስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ላይ የተመለከተው።
የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን ጥቃት ለማስቆም ያደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባም አምንስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አድርጓል።
በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እየተካሄደ ባለው የአማራ ተወላጆች ጥቃት በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ባህርዳርና ቆቦ በመሰደድ የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ላይ ናቸው።