በሻሸመኔ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጸመ

ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ቁጥራቸው 13 የሚጠጋ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት አቶ በየነ ሞርሲ፣ ሳምሶን ራቦ፣ አበራ መቲቦ እንዲሁም በማዘጋጃ ቤት ውስጥ ሀላፊ የሆነ አቶ ዳዊት ደጮ የተባሉት ግለሰቦች ” አብዲ ሁንዳ” እና ሀምሌት የተባሉ የቤትና የንግድ ማህበሮችን መስርተናል በሚል ከግለሰቦቹ በነፍስ ወከፍ እስከ ከ10 ሺ ብር በድምሩ ከ194 ሺ ብር ያላነሰ ገንዘብ ተቀብለዋል።

ግለሰቦቹ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አባ ዱላ ገመዳ ለደሀ ቤተሰቦችና ለጎዳና ተዳዳሪዎች ቤት መስሪያ እና የንግድ ድርጅት ማቋቋሚያ  የሚውል ቦታ ፈቅደዋል፣ በማለት በመጀመሪያ 2 ሺ 400 ብር ለሱቅ፣ ቀጥሎም ህንጻውን ለማሰራት 8500 ብር ተቀብለዋል።

የመዘጋጃ ቤቱ ሰራተኛ ግለሰቦችን በቢሮው  ጠርቶ  ፋይላቸው ምክትል ከንቲባው ቢሮ ውስጥ በሚስጢር መያዙን እንደገለጻቸው ፣ ከዜ በሁዋላ ምክትል ከንቲባው ጉዳዩን እንደማያውቁት በመናገራቸው ግለሰቦቹ ሊጋለጡ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የነጋጋርናቸው ጠበቃው አቶ ሻሮ በቀለ “ሊቀመንበሩ ብቻ ገንዘቡን በከፊል መቀበሉን ማመኑን ” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱም የበርካታ ሰዎችን ምስክርነት የሰማ በመሆኑ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት  በ5 ሺ ብር ዋስ ተለቀዋል ።