(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 29/2010) በሸካ ዞን የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢው አመራሮች የሚፈጸምባቸውን የአስተዳደር በደል በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።
በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችና የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ተወላጆች በሸካ ዞን አስተዳደር የሚደርስባቸውን በደል በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውመዋል።
በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በቅርቡ 6 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
በሸካ ዞን የተለያዩ ብሔረሰቦች በፍቅርና በመተሳሰብ ለዘመናት አብረው ኖረዋል።
ባለፉት 27 አመታት በነበረው ብሔርን መሰረት ባደረገው ፖለቲካ ግን ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች የአስተዳደር በደል እንደደረሰባቸው በምሬት ይናገራሉ።
በሸክቾ ብሄረሰብ ስም የዞኑ አስተዳደርን በብዛት የተቆጣጠሩት አመራሮች በሌሎች ላይ ግፍና በደል ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።
የተለያዩ ግፍና በደል የደረሰባቸው ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች መታሰራችን ይብቃ በሚል በቴፒ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
ለአካባቢው ግጭቶች መንስኤ የሆኑት የፖለቲካ ደላሎች መሆናቸውን የሸካ ተወላጅ የሆኑት የለንደን ነዋሪው አቶ አየለ ለኢሳት ገልጸዋል።
አቶ አየለ ስለ ችግሩ ሲናገሩ በአካባቢው የፖለቲካ ደላሎች ችግር እንጂ በብሔር መካከል ችግር የለም ብለዋል።
በሸካ ዞን የመዠንገር ነዋሪ የሆኑትና በአሜሪካ ኑሯቸውን ያደረጉት አቶ ቢኒያም እንደሚሉት ደግሞ በአካባቢው ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ለሕዝብ ብሶት ምክንያት ነው።
እናም መፍትሄው የበታች አመራሮችን አንስቶ በሌሎች መተካት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሸካ ዞን ያለውን የሕዝብ እሮሮ ለመፍታት የፌደራልና የሕዝብ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ቢያመሩም ችግሩ ግን አሁንም እንዳልተፈታ የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ተናግረዋል።