በሶማሊ ክልል የኮካ ኮላ ምርት እንዳይገባ ታገደ

ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ የኢሳት ምንጭ እንደገለጸው ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ የኮካ ኮላ ምርት ወደ ክልሉ እንዳይገባ በመታገዱ ነዋሪው ህዝብ ከሶማሊላንድ እየታሸገ በኮንትሮባንድ የሚገባውን ኮካ ኮላ ለመጠቀም ተገዷል። ኢትዮጵያ በሚገኘው በኮካ ኮላ ድርጅትና በክልሉ መንግስት መካከል ልዩነት መፈጠሩም ታውቋል።

ቀደም ብሎ በክልሉ የኮካ ምርትን የሚያከፋፍለው የታዋቂዋ ባለሃብት የወ/ሮ ሱራ ድርጅት ሲሆን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ግለሰቡዋ የኦጋዴን ተወላጅ ባለመሆናቸው ለወ/ሮ ሃዋ እንዲሰጥ በመወሰናቸው ነው።

ወ/ሮ ሃዋ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ቁጥር አንድ ባለሃብት እየሆነች የመጣች የጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል የፍቅር ጓደኛ ናት።

ወ/ሮ ሱራ ከ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር በሽርክና በመስራት ጫት ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊላንድ በማመላለስ ከፍተኛ ሃብት አካብታለች። ግለሰቡዋ ሶማሊላንድ ላይ ግንባታዎችን ማካሄዱዋን እንደሰበብ የተጠቀሙበት የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ ኮካን የማከፋፈሉን ስራ ከወ/ሮ አዜብ የንግድ ሸሪክ ወደ ጄኔራል ዮሃንስ ገብረመስቀል የፍቅር ጓደኛ አዙረዋል።

መስተዳድሩ የኮካን ምርት ወ/ሮ ሃዋ የማታከፋፍል ከሆነ ኮካ ኮላ በክልሉ መሰራጨት የለበትም የሚል አቋም መያዙን ተከትሎ፣ የኮካ ኮላ መስሪያ ቤት ለሁለቱም ባለሀብቶች መስጠቱን ትቶ ራሱ ማከፋፈል እንደሚጀምር መግለጹ ታውቋል።

በክልሉ መሪ በአቶ አብዲና በወ/ሮ አዜብ መስፍን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ወ/ሮ ሱራ የኮካ ኮላ ማከፋፈሉን ስራ እንድትነጠቅ ከማድረጉም በላይ ወደ ሶማሊላንድ ስትልከው የነበረውንም ጫት  ከወ/ሮ ሃዋ ጋር በየሁለት ሳምንቱ ተካፍለው እንዲልኩ በመወሰናቸው ወ/ሮ ሱራን ከጫዋታ ውጭ እያደረጉዋቸው ነው።

ወ/ሮ ሃዋ በጅጅጋ፣ በደገሃቡርና በመቀሌ የተለያዩ ግንባታዎችን እያካሄዱ ነው። ጄ/ል ዮሃንስ በክልሉ ውስጥ በአዛዥነት ይሰሩ በነበረበት ወቅት የተለያዩ የመከላከያ ኮንትራቶችን ለወ/ሮ ሃዋ በመስጠት በአንድ ጊዜ ከኢንቨስተሮች ተራ እንድትገባ አድርገዋታል።

ወ/ሮ ሱራ በበኩላቸው ከጠ/ሚንስትር መለስ ሞት በሁዋላ በክልሉ ያላቸው ተሰሚነት እየቀዘቀዘ በመምጣቱ ትኩረታቸውን ሁሉ ሶማሊላንድ ላይ ለማድረግ ተገደዋል።

በጣም የሚገርመው ይላል ምንጫችን ኮካ ኮላ በህጋዊ መንገድ እንዳይገባ ከተደረገ በሁዋላ በኮንትሮባንድ ከሶማሊላንድ እያስገቡ የሚሸጡት ጅጅጋን የሚያስተዳድሩት የህወሀት የመከላከያ አዛዦች ናቸው። እነዚህ አዛዦች ያለምንም ከልካይ ኮካ ኮላ በማምጣትና በማራገፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ እያጋበሱ ነው።

ጄ/ል ዮሃንስ ጄ/ል ሳሞራ የኑስን ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለከተማ  ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ዘመናዊ የንግድ ድርጅት መገንባታቸውን ኢሳት በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ማቅረቡ ይታወቃል።

የህወሃት የመከላከያ አዛዦች ጅጅጋን የሃብት ማግኛ ማእከላቸው አድርገው እንደሚቆጥሯት የክልሉ ተወላጆች ሲገልጹ ይሰማል።

በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ የክልሉ የገጠር ከተሞች በአንበጣ መንጋ መወረራቸው ታውቋል። የክልሉ መንግስት እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱንም የደረሰን መረጃ ይገልጻል።