መንግስት የመንግስት ተሽከርካሪዎች በኮድ 4 ሰሌዳ ቁጥር ብቻ እንዲጠቀሙ መመሪያ አወጣ።

ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት መመሪያውን ያወጣው በግለሰብ ታርጋዎች በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች መበራከታቸውን በተመለከተ ዘገባው በኢሳት ከቀረበ በሁዋላ ሲሆን፣ ታዛቢዎች ግን አዲሱ መመሪያ ይስሙላ ነው ይላሉ።

ኢሳት የምንጮቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል የመመሪያውን ቅጅ ይፋ ባያደርግም ከአፌዲሪ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር መ/401/653/2 የተላለፈው ሠርኩላር  የመንግስት መስሪያ ቤት ተሽከርካሪዎች ከኮድ ቁጥር 4 ውጭ መጠቀም እንደማይችሉ በጥብቅ ያሳስባል።

ደብዳቤው ” በመንግስት ህግና ደንብ መሰረት በኮድ 4 ሠሌዳ መጠቀም ከሚገባቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንዳንዶች በኮድ 2፣ በኮድ 3 እና በሌሎች በተለያዩ ሰሌዳዎች በመጠቀም ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል ” ካለ በሁዋላ ” በመንግስት ህግና ደንብ መሰረት የመንግስት ተሽከርካሪዎች በኮድ 4 ብቻ እንዲጠቀሙ እንዲደረግ የመ/ቤት ኃላፊዎች አርአያ በመሆን ለተግባራዊነቱ ትኩረት እንዲሰጡ፣ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮም በዚህ መሰረት ክትትል እንዲያደርግ እናሳስባለን” ሲል ይደመድማል።

በአሁኑ ወቅት የፌደራል ፖሊስ፣የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ሌሎች የፌደራል ደህንነት መ/ቤቶች በግልጽ በሚታወቅ ሁኔታ በህዝቡ መካከል፣በግለሰብ ቤትና በመንግስት መስሪያ ቤት ቢሮዎች እየገቡ ሰላማዊ ሰውን አፍነው የሚወስዱት በኮድ 4 የመንግስት መኪና ሳይሆን ከዚህ ውጭ በሆኑ ኮድ 35፣ ኮድ 3፣ እና ኮድ 2 የሰሌዳ ቁጥር ባላቸው የመንግስት ተሽከርካሪዎች ነው፡፡

መንግስት ለደህንነት ስራ በሚል የደህንነት ሰራተኞች ከኮድ አራት ውጭ ያሉ ቁጥሮችን እንዲጠቀሙ ፈቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደህንነት ሰራተኛውን ከፖሊሱ ወይም ከወታደሩ ለመለየት ችግር እየተፈጠረ መምጣቱና በእነዚህ መኪኖች የሚፈጸመው ወንጀል እየተባባሰ መሄዱ መንግስትን ራሱን አደጋ ላይ ጥሎታል።

በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል 285 መኪኖች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች መገዛቱ ያደረሰውን  የፖለቲካ ኪሳራ ለማስተካከል በሚመስል መልኩ መመሪያው መዘጋጀቱንም የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።