በሶማሊ ክልል በሚሊሺያዎች እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት 11 ሰዎችና ቁጥራቸው ያልታወቁ ፖሊሶች ተገደሉ

መስከረም ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በክልሉ መንግስት እየተደገፈ የተለያዩ የስብአዊ መብቶችን በመጣስ የሚታወቀው የሶማሊያ ሚሊሺያ ታጣቂ ሀይል ሰሞኑን ከሀሺ ወረዳ ህዝብ ጋር በፈጠረው ግጭት 11 ሰዎችን ሲገድል፣ ከሚሊሺያዎች ወገን ደግሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ይሁን እንጅ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

በኦጋዴን አካባቢ ብቻ ሳይሆን ወደ አፋር አካባቢዎች በመንቀሰቃስ በመንቀሳቀስ የተለያዩ ግጭ  ቶችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚፈጽመው ይህ የሚሊሺያ ሀይል በክልሉ መንግስት እንደሚደገፍ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

ታጣቂው ሀይል በሀሺም ወረዳ ውስጥ   ሴቶችን ሲደፍርና  ሱቆችን ሲዘርፍ መቆየቱን የአካባቢው ተወላጆች ገልጠው፣ ለአሁኑ ግጭት መንስኤ የሆነው ግን ታጠቂ ሀይሉ አንድ መምህርን እና አንድ ታዳጊ ልጅን በጥይት እንዲሁም አንድ በእድሜ የገፉ ሴትን በመኪና ከገደለ በሁዋላ   ህዝቡ መሳሪያውን በማንሳት ፊት ለፊት በመግጠሙ ነው።

ህዝቡ በተጣቂ ሀይሉ ላይ በወሰደው እርምጃ በርካታ ታጣቂዎች ሲገደሉ፣ ከህዝቡ ወገን ደግሞ 11 ሰዎች በታጣቂው ሀይል ተገድለዋል ፣ በርካቶችም ቆስለዋል።

በግጭቱ መሀል  የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ከታጣቂው ጎን ሆነው አመራር ሲሰጡ መዋላቸው የአካባቢው ተወላጆችን ግራ አጋብቶአቸዋል።

ጉዳዩን የአለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀውና የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ነዋሪዎች ተማጽነዋል።

በሶሚሊ ክልላዊ መንግስት የሚደገፈው ሚሊሺያ፣ ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል እየዘመተ ዝርፊያ ሲያካሂድና በርካታ ንጹህ ሰዎችን ሲገድል መቆየቱን መዘገባችን ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide