እስክንድር ነጋ የታሰረበት ፩ኛ አመት ታሰቦ ዋለ

(Sept. 17) ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሌሎች የህሊና እስረኞች የታሰሩበትን አንደኛ አመት የሚያስብ ዝግጅት ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 4 ቀን በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ።
በዚህ የዋሽንግተን ዲሲ አምነስቲ አለማቀፍ ቅርንጫፍ ደጋፊዎችና ፍሪ እስክንድር ነጋ ባዘጋጁት ዝግጅት ላይ፤ የእስክንድር ነጋን ቤተሰቦች ጨምሮ አያሌ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው የሻማ ማብራት ስነ-ስርአት አካሂደዋል።
የዝግጅቱ አስተባባሪ፤ ወ/ት አዜብ የዝግጅቱን ዓላማ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ አያሌ የህሊና እስረኞችን እንዲፈቱ በኢትዮጵያና፤ በአሜሪካ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ነው ስትል ተናግራለች።
በመሀል ዋሽንግተን ዲሲ  በሚገኘው የአፍሪካ አሜሪካዊያን የሲቪል መብቶች ትግል መታሰቢያ ሀውልት ዙሪያ በተካሄደው ዝግጅት ላይ፤ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚገኙ አያሌ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች፤ በሚቀጥለው ወርም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን የመሬት ንጥቂያ በተመለከተ ተመሳሳይ ዝግጅት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።
እስክንድር ነጋ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ሕዝብን ለአመጽ ለማነሳሳትና መንግስትን ለመጣል ይጎተጉታል በሚል ክስ ባለፈው አመት መስከረም ሶስት ቀን ታስሮ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፍ/ቤት ባለፈው ሀምሌ የአስራስምንት አመት እስራት ፈርዶበታል።
እስክንድር ነጋ፤ አንዱአለም አራጌና ሌሎች እስረኞችም በአሁኑ ሰዓት በቃሊቲ እስር ቤት ይገኛሉ። እስክንድር ነጋ፤ የዚህ አመት የፔን አሜሪካ ሽልማት አሸናፊ ሆኖ፤ ባለቤቱ ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል በኒው ዮርክ ሽልማቱን መቀበሏ ይታወሳል።