በሲዳማ ዞን የአለታ ጩኮ ወረዳ ህዝብ በውሃ እና መብራት ማጣት እየተሰቃየ ነው

መጋቢት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወረዳው ውሃ ከ15 ቀን በላይ በመጥፋቱ ከጉረቤት ቀበሌያት እየተቀዳ የሚመጣው ንፅህናው ያልተጠበቀ አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ 10 ብር እየተሸጠ ሲሆን ፣  ይህንኑ ውሃ በአህያ ጋሪ ከተማ ውስጥ ለመግዛት ነዋሪዎች ቀድመው ለመክፈል ይገደዳሉ ።

አንዲት የጪኮ01 ቀበሌ ነዋሪ የሆነችና በሰው ቤት የቀን ስራ ሰርታ የምትተዳደር ሴት  ” እቤቴ የአንድ አመት ልጅ አለኝ ልጄ በውሃ ጥም እየሞተ ነው ይኸው አንድ የታሸገ ውሃ በእጅዋ ይዛ እያሳየች ይህንን ለልጄ ስል በ15 ብር ገዛሁ ግን አቅሜ እንኳን ለታሸገ ውሃ ለዳቦም አልበቃ” ብላለች ።

ሌላውም አርሶ አደር ልጆቼን ከትምህርት ቤት አስቀርቻለሁ ምክንያቱም ውሃ በሌለበት አምኜ ከተማ ልጆቼን አልክም ብለዋል ። በአንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ቤት ውሃ ለሊት ለሊት የሚመጣ ሲሆን ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት የውሃ ጵ/ቤት ሃላፊ አቶ መኩሪያ፣ ችግሩ የተከሰተው ዋናው የውሃ ታንከር የሚያንቀሳቅሰው የኤሌክትሪክ መስመር በመበላሸቱ ምንም ማድረግ አልችልም በማለት ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል ።

የወረዳው አስተዳደር ጉዳዮን ለመፍታት ያደረገው ሙከራ የለም የሚሉት ነዋሪዎች ለራሱ ቢሮ ጄኔሬተር በመግዛት እና የታሸገ ውሃ ለሃላፊዎች በማቅረብ የህዝቡን ችግር ረስቶታል ሲሉ መናገራቸውን የአካበባው ወኪላችን ገልጿል።