በአማራ ክልል የተሰሩ የገጠር መንገዶች ጥራት ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ችግሩን አምኗል፡፡

መጋቢት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓም. በሚቆየው የአማራ ክልል ምክር ቤት 4ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በቀረበው  የግማሽ አመት ሪፖርት፣  ከየዞኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት በቀረቡት ጥያቄዎችንና ቅሬታዎች በክልሉ በተገነቡ የገጠር መንገዶች አሰራር ላይ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ መንገዶች ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ በመፈራረስ ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በሰሜን ጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች በምስራቅና ምእራብ ጎጃም ልዩ ልዩ ቦታዎች ችግሮች እንደተከሰቱ የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴ አባላት የሚሰሩት የጥገና ስራዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው ፤ በዩራፕ (ሁሉ አቀፍ ገጠር መንገድ ስራ) የተደራጁ ወጣቶች በአግባቡ ባለመስራትና በመበታተናቸው ስራዎች በተገቢው ሁኔታ አለመፈጸማቸው፤

-በዩራፕ አቅም የማይሰሩ ድልድዮችን ለነዚህ ጀማሪ የመንገድ ስራ ተቋራጮች በመሰጠቱ ድልድዮች በወቅቱ ባለማጠናቀቃቸው መንገዶች በጅምር መቅረታቸው፤ ተቋራጮችና አማካሪዎች ባለባቸው ያቅም ማነስና ውስንነት በየአካባቢው መነሳቱ ለሚከሰቱ የመንገድ ላይ ችግሮች አንድ ምክንያት መሆናቸው፤

-በተለያዩ ወረዳዎች የሚከሰቱ መንገዶች የዲዛይን ችግር ቢኖርባቸውም ይህን ከማስፈጸም አኳያ ለማሳተካከል አለመሞከሩ፤ መንገዶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እድሳት እንዲደረግላቸው አለመደረጉ በትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማድረሱ ፤

-ተቋራጮች ኮንትራቱን ካሸነፉ በኋላ  ´ ቦታው አስቸጋሪ ነው ´ በሚል ሰበብ ስራው አዋጭ አይደለም በማለት ኮንትራታቸውን ቢሰርዙም ጉዳዩን ተከታትሎ የሚያስፈጽምና ርምጃ የሚዎስድ የመንግስት አካል ባለመኖሩ ድርጊቱ በተከታታይ መከሰቱ፤

-የክልሉ መንግስት በየዓመቱ በጀት በመያዝ የሚያሰራቸውን መንገዶች ለህዝቡ አስቀድሞ አለማሳወቅ እና በጀቱ ተይዞላቸው በተለያዩ ችግሮች መሰራት ካልቻሉ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ምክንያታቸውን በማሳወቅ በኩል እጥረት በመኖሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥያቄ መፍጠሩ፤ የሚሉ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ቀርበዋል፡፡

በቀረቡት ጥያቄዎች ዙርያ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት የገጠር መንገዶች ባለስልጣንዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ስማቸው  ንጋቱ  “በጥገና በኩል የተነሳው ጉዳይ ለድርጅቱ ፈተና ነው፡፡ይህም የበጀት ችግር አለብን፡፡” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ማህበራት ተበተኑ በሚል ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱም ከ30 በላይ ማህበራት ስራቸውን አቋርጠው መበተናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ ገጠር መንገዶች ስራ ላይ በማህበር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አብዛኛው ተቋራጮችም ሆነ አማካሪ መሃንዲሶች የረዢም ጊዜ የመንገድ ስራ ልምድ የሌላቸው ፣የባስልጣናት ቤተሰቦች እና በመስሪያቤቱ ባለሙያዎች ጋር በሽርክና የሚሰሩ በመሆኑ በየጊዜው በሚሰሩ መንገዶች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታ ሲቀርብ ይሰማል፡፡

የክልሉ የገጠር መንገድ ስራ ባለስልጣን ኃላፊ ከአሁን በፊት በድርጅቱ የሚካሄዱ የሙስና አሰራሮችን ለመከላከል እንዳልቻሉ ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ መሰረት በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል፡፡