ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ ክልል የመንግስት ባለስልጣናት ከክልሉ ባለሀብቶች ጋር ከጥቅምት 9 እስከ 10 ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ነው ነባር የህወሀት ታጋዮች አዲሱን የመሬት ሊዝ ዋጋ አምርረው የተቃወሙት።
” የግብር ኢንቨስትመንት የስራ እንቅስቃሴና የ2005 እቅድ የጋራ ውይይት” በሚል አጀንዳ የተካሄደውን ስብሰባ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞድ ኦቦንግ፣ ከፌደራል መንግስቱ ተወክለው የመጡት የኢንቨስትመንት ሃላፊው አቶ ኢሳያስ እንዲሁም የክልሉ የግብርና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ጆን መርተውታል።
በውይይቱ ወቅት ከፍተኛውን ትኩረት የሳበው አዲሱ የመሬት የሊዝ ዋጋ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በሄክታር 33 ብር ይከፍሉ የነበሩ ባለሀብቶቹ በአዲሱ ተመን 111 ብር እንዲከፍሉ ተደርጓል።
ባለሀብቶች “በድንብ ሳንቋቋም ፣ ስራ በወጉ ሳንጀምር በአንድ ጊዜ ይህን ያክል ጭማሪ ማድረግ ” ለስራ የሚያበረታታን አይደለም በማለት አዲሱን ተመን ተቃውመዋል።
የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስባቸው ባለሀብቶች ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
አንድ ወደ ኢንቨስተርነት የተለወጠ የህወሀት ነባር ታጋይ የጠየቀው ጥያቄ በመደረኩ ውስጥ ከፍተኛ አግራሞትን መፍጠሩን ስብሰባውን የተከታተሉ አንድ ባለሀብት ለኢሳት ገልጠዋል። የህወሀት አባሉ ” እኛ እዚህ የተሰብሰብነው አብዛኞቻችን ነባር ታጋዮች ነን። ወደዚህ ስራ የገባነው ከትግል በሁዋላ ነው። ምንም አቅም እንደሌለን እየታወቀ እንዲህ አይነት ጭማሪ ማካሄዱ ተገቢ አይደለም። ለደህንነታችን ማስጠበቂያም የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ቢሰጠን ጥሩ ነው። መሳሪያ የለም እንዳይባል እኛ በሻቢያ ወረራ ጊዜ ምን ያክል መሳሪያ እንደተሰበሰበ እናውቀዋለን።” በማለት ጠይቀዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ለታጋዩ በሰጡት መልስ ” ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት እንሞክራለን። ደህንነታችሁን በማስጠበቅ አንጻር ከህዝቡ ጋር እየተወያየን ለመፍታት እንሞክራለን።” ብለዋል። የሊዝ ዋጋ ጭማሪው ተጠንቶ የቀረበ መሆኑን ፣ ይሁን እንጅ ተጨማሪ ውይይት ካስፈለገ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ከአቶ ሽፈራው ተክለማርያም ጋር እንደሚወያዩበት ተናግረዋል።
በክልሉ ውስጥ ከተመዘገቡት ከ600 ያላነሱ ኢንቨስተሮች ( ባለሀብቶች) ውስጥ ወደ ስራ የገቡት ከ150 የማይበልጡ ሲሆን አብዛኞቹ ነባር የህወሀት ታጋዮች ናቸው።
አዲሱ የሊዝ ዋጋ የውጭ አገር ባለሀብቶችንም እንደሚመለከት ለማወቅ ተችሎአል።