በኢትዮጵያ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ በውጭ አገር ባለሃብቶች የሚካሄደው የመሬት ዘረፋና ሽሚያ ተወላጆቹን ለመፈናቀልና ለሞት እያጋለጠ ነው ተባለ።

 

ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል  እንደገለጸው በ አ ካባቢው እየተፈፀመ ያለው ድርጊት ነዋሪዎች መሬታቸውን እንዳያርሱ እንቅፋት በመፍጠር በርካታዎችን በችጋር እያመሰና ‹‹ሞታቸውን እንዲጠብቁ›› እያደረገ ነው ።

 

ድርጅቱ ይህን ያለው፤በመላው ዓለም ላይ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር  ኦክቶበር 16 ቀን የሚከበረውን  የ “ዓለም የምግብ ቀን”ን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

በታችኛው ኦሞ ሸለቆ በኢትዮጵያ  ኢሰብአዊ ገዥዎች አማካይነት በሚካሄድ የመሬት ዝርፊያ  ፤ቀደም ሲል ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩ 200 000 የ አካባቢው ነዋሪዎች፤ የምግብ ዋስትና አጥተው ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን የድርጅቱ ጥናት ያመለክታል።

ገዥው ፓርቲ በልማት ስም  ከሀብትና ይዞታቸው ከሚያፈናቅላቸው ነዋሪዎች መካከል፤የሱሪ፤ የሙርሲ፤ የቦዲ እና የክዌጉ ብሔረሰብ አባላት  እንደሚገኙበትም- ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል አመልክቷል።

<<ገዢው መንግስት በታችኛው ኦሞ ላይ አትራፊ የሚለውን ልማት አካሄዳለሁ በማለት እነዚህን ዜጎች ከቀያቸውና ከንብረታቸው አስገድዶ እያፈናቀላቸው ነው።  የደህንነት አባላት ከብቶቻቸውን በጉልበት እየነጠቁና እየዘረፉ ከመኖሪያቸው በማስወጣት እያባበረሯቸው ነው>>ብሏል ሰርቫይሻል በመግለጫው።

አንድ የሙርሲ ብሔረሰብ ተወላጅ ለድርጅቱ ሲናገር፦ <<የገዢው መንግሥት ሰዎች የደረሰ በቆሏችንን እየነቀሉ ወደ ወንዙ እየጣለብን ነው፡፡ እርሻዎቻችንን  መንጥረውና ምርቶቻችንን ነቃቅለው ወደ ወንዝ ጨምረውታል፡፡በበኩሌ አሁን የቀረኝ ጥቂት ጥሬ ነው። እሷ ካለቀች በሁዋላ የምጠብቀው፤ ሞትን ነው>> ብሎአል፡፡

ሌላው የሱሪ ተወላጅ ደግሞ፦ ‹‹አሁን ቦታውን አጥርተው እኛንም አባረው ጨርሰዋል>>ካለ በሁዋላ ፦ <ለመሆኑ የናንተ ተወካይ ነኝ የሚለን መንግስት ለምንድን ነው መሬታችንን የሚሸጥብን?>> በማለት በሀዘን ጠይቋል።

በማከልም፦<< አሁን ለከብቶቻችን ሣር የለም፤ በግድ <ሰፈራ>  የተባልነው ሁሉ እየተራብን ነው፡፡ ለችጋር ተጋልጠናል፡፡ ስለምግብ በጣም ሃሳብ ገብቶናል፡፡ አሁን ፤ቁጡ እና ተስፋ ቢሶች ሆነናል፡፡››ብሏል።

ለደህንነቷ ስትል ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች  አንዲት የኦሞ ሸለቆ አካባቢ ነዋሪ የሆነች  የሙርሲ ተወላጅ  ደግሞ ከይዞታና ሀብታቸው  በግዳጅ መፈናቀላቸውን ተከትሎ ባጋጠማቸው ረሀብና ችግር ቤተሰቧቿ እንዳለቁባት ተናግራለች።

የኦሞ ሸለቆ አካባቢ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ማዕከል-ዩኔስኮ የተመዘገበና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ቦታ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት  በአካባቢው የግልገል ጊዜ ቁጥር ሶስት ግንባታን ሲያካሂድም ሆነ አሁን በቦታው ሰፊ  የስኳር ልማት ተክል ለማካሄድ እንቅስቃሴ ሲጀምር ስለ ጉዳዩ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አልተመካከረም በሚል በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና  በአካባቢ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዘርበታል።

የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር  ስቲቭን ኮሪ ‹‹በዓለም የምግብ ቀን ወቅት የዓለም ሕዝብ ሊገነዘበውና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሳቸውን ተማምነውና ራሳቸውን ችለው  ለመኖር የሚችሉትን  የኦሞ ሸለቆ ነገዶች ለማፈናቀልና ለማጥፋት መነሳሳቱን ነው>> ብለዋል።

የ ኢትዮጵያ መንግስት በጀመረውም እንቅስቃሴ ብዙዎች ለምግብ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ዓለማቀፉ ህብረተሰብ ሊገነዘብ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

ስቲቨን ኮሪ አክለውም፦<እነዚህ ነገዶች ለዘመናት መሬቶቻቸውን ለምግብ ምርትና ለከብቶቻቸው ግጦሽ ማብቀያ ሲጠቀሙ የቆዩ ናቸው። ይህ  ሂደትም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ ነው፡፡አሁን  ግን መሠረታዊ መብታቸው በጭካኔ መንገድ እየተገፈፈ፤ ለፍርሃትና ለሞት እየተዳረጉ ነው›› ብለዋል::

ድርጊቱ የሙርሲን፤የቦዲን፤ እና የጉዌጉን  ጎሳዎችን  የኑሮ ዋስትና በማሳጣት ለዘመናት ከኖሩበት  አካባቢያቸው  ለማጥፋት የተያዘ ዕቅድ ይመስላል ሲሉም ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ መንግስት ድርጊት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተር ስቲቨን ገለፃ፤እነዚህን ጎሳዎች ለዘመናት አያት ቅድመአያቶቻቸው ኖረውበት ካስረከቧቸውና ንብረት መስርተው ቤተሰብ አፍርተው ከሚኖሩበት ቅድመ- ርስታቸው መፈናቀል ማለት  ጉዳቱ መጠነ ሰፊ ነው።

በመጀመሪያ አሁን እንዲሰፍሩ የሚባልበት ቦታ ተወልደው ካደጉበት አካባቢ በብዙ መልኩ የተለየ ከመሆኑና፤ ዘርተው ለማብቀልና ለመቋቋም አዲስ መጦች ከመሆናቸው አንፃር ከመሬቱ ምርታማነት ባህል ጋር ሊተዋወቁ አይችሉም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከብቶቻቸውም የኖሩበትን ለቀው ወደ አዲስ ቦታ ሲሰማሩ ምን ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ባለመታወቁ  ከፍ ያለ ድንጋጤና ፍርሀት ውስጥ መውደቃቸውን አስረድተዋል።

ዳይሬክተሩ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም፡_<<ምንም ይሁን ምን ፤የዜጎችን ጥቅም ማስቀደም የሚገባው መንግሥት፤ እነዚህን እርቃናቸውን እየኖሩ ዳር ድንበራቸውን ግን ከጠላት ለዘመናት ሲጠብቁ የቆዩትን እና <ደመወዝ ስጡን- ቀለብ ቁረጡልን> የሚል ጥያቄ ፈፅሞ አንስተው የማያውቁትን ዜጎች፤ ጠብ ያለሽ ዳቦ ብሎ ካሉበት ድረስ ሄዶ ነገር መፈለጉ ለማን እንደሚጠቅምና ማንን እንደሚጎዳ ማሰብ፤ እንዴት ይሳነዋል?”ሲሉ  በአጽንኦት ጠይቀዋል