አቶ ሀይለማርያም ካቢኔያቸውን መሰየም አልቻሉም

ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዲሶቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻና አለመግባባት ሊፈታ ባለመቻሉ፤ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን ለመሾም አለመቻላቸውን በግንባሩ ውስጥ የሚገኙ የኢሳት ምንጮች ጠቆሙ።

አቶ ሀይለማርም ደሳለኝና አቶ ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው በተመረጡበት ዕለት ምሽት በሂልተን ሆቴል በጋራ መግለጫ የሰጡት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ሬድዋን ሁሴን ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ የራሳቸውን ካቢኔ ያዋቅራሉ ማለታቸው ይታወሳል።

ይሁንና አቶ ሀይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወራት እየተቆጠሩ ቢሆንም ፤እስካሁን ድረስ የራሳቸውን ካቢኔ ማዋቀር አልቻሉም።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በሹመቱ ማግስት፦< እንደ ብዙሀን ወኪልነቴ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን አለማግኘቴ አግባብ አይደለም> በማለት የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) ያነሳው ተቃውሞ እስካሁን መቋጫ ሊገኝለት አለመቻሉ እንደሆነ ምንጮቹ ጠቁመዋል።

በ ኦህዴድ ውስጥ የተነሳውን ተቃውሞ ለማዳፈንና ለማስቀረት በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ሹመት ተገቢ ስለመሆኑ በከፍተኛ ካድሬዎች አማካይነት እስከ ታች ድረስ ካሉ የድርጅቱ አባላት ተከታታይ ውይይቶች ሲደረጉና ሰፊ ሥራዎች ሢሰሩ መቆየታቸውን  ምንጮቹ ጠቅሰዋል።

ይሁንና በ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሳይቀር እርምጃ በመውሰድ የታገዘው ረዥም ጊዜ የወሰደ ውይይት  የኦህዴድን አባላት ከልብ በማሳመን በኩል የተሳካ ነው ለማለት የማይስደፍር ነው ያሉት ምንጫችን፤ የአቶ ሀይለማርያም የካቤኔ ሹመት የዘገየውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀጣይ ችግር እንዳይፈጠር በሚል ነው ብለዋል።

<የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበርን ያላገኘው ኦህዴድ በአቶ ሀይለማርያም ካቢኔ ውስጥ በምን ሊወከል ይችላል?>የሚለው ትልቅ የራስ ምታት መፍጠሩን  ምንጫችን ጠቅሰዋል።

ከሁለቱ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ  አንደኛቸውንም ያጣው ኦህዴድ ፤ከተቀሩት የካቢኔ ሹመቶች የተሻለ ቦታ የሆነውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ቦታ ሊያገኝ እንደማይችል ምልክቶች እየታዩ ናቸው ያለው የኢሳት ምንጭ፤ ይህም በድርጅቱ አባላት ዘንድ ተከታይ ተቃውሞ ሊያስነሳ እንደሚችል ስለተገመተ ከወዲሁ ሰፊ የማሳመን ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝና የካቢኔ ሹመቱም የማሳመኑ ሥራ እስኪጠናቀቅ ሊዘገይ ግድ መሆኑን አስረድቷል።

ላለፉት 21 ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ተቆጣጥሮ የቆየው ህወሀት፤ በአዲሱ የካቢኔ ሹመትም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርነቱ የራሱ እንደሆነ መወሰኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዙ ህዝብ የሚወክለው ኦህዴድ  <የተሻሉ ናቸው> ከሚባሉት የስልጣን ቦታዎች አንድኛቸውን ሳያገኝ የይስሙላ ቦታ በሆኑት በፕሬዚዳንትነትና በመከላከያ ሚኒስትርነት መሰየሙ፤ በግንባሩ ውስጥ የዲሞክራሲ ማዕከላዊነት አለመኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ።