በርካታ ባለስልጣናት ሰዎችን በመኪና ገጭተው ቢገድሉም እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ/ም) የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአገዛዙ ባለስልጣናት ሰዎችን በመኪና እየገጩ ቢገድሉም እስከዛሬ ግን ለፍርድ ቀርበው ሲቀጡ አልታዬም።
ወብሸት ገብረ-እግዚአብሄር የተባለው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ መስራችና የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ የነበረና በልደታና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አንድ በድህነት ውስጥ የሚገኙ እናት በመኪና ገጭቶ ቢገድልም ፣ ለፍርድ ቀርቦ አያውቅም።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ዶ/ር አጸደ አሰፋ ቸርችል ጎዳና ላይ አንድ ወጣት በመኪና ገጭታ ብትገድልም እስከዛሬ ለፍርድ አልቀረበችም።
እንዲሁም የህዳሴ ጋዜጣ ም/አዘጋጅ የነበረውና የህብረተሰብ ተሳትፎ ጽ/ቤት ሃላፊ ሆኖ የተሾመው አቶ ዋቸሞ ጴጥሮስ በተመሳሳይ መንገድ በመኪና አንድ ሰው ቢገድልም ለፍርድ አልቀረበም።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች ወንጀሉን መርምረው ባለስልጣኖቹ እንዲከሰሱ ሙከራ በሚያደርጉም፣ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ተወልደ ገ/ ጻዲቅ በፖሊሶቹ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደርና በማስፈራራት ባለስልጣናቱ ለፍርድ እንዳይቀርቡ ማድረጋቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።