አዲ ረመጥ በሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ላይ የቦንብ ጥቃት ተፈጸመ

አዲ ረመጥ በሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ላይ የቦንብ ጥቃት ተፈጸመ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ምንጮች በፎቶ ግራፍ አስደግፈው በላኩልን መረጃ ባለፈው አርብ አዲ ረመጥ ላይ በሚገኘውና የህወሃት ንብረት በሆነው ሱር ኮንትስራክሽ ኩባንያ ንብረት ላይ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ የቦንብ ጥቃት ተፈጽሞ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ጥቃቱ የደረሰው የሱር አማካሪ በሆነው ልደት ኮንሳልታንት የግል ድርጅት ላይ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በጥቃቱ የተጎዳ ሰው አለመኖሩም ታውቋል።
ይህን ተከትሎ ወታደሮች ህዝቡን ሰብስበው ጥቃቱን የፈጸሙትን ሃይሎች እንዲያጋልጥ ለማሳመን ቢሞክሩም ሳይሳካለቸው ቀርቷል። ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው የታወቀ ነገር የለም።
በዚሁ ቀን ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ሰቲት ሃውስ ፊት ለፊት ከሚገኘው ህብረት ሆቴል ውስጥ በደረሰ ጥቃት አንድ የመከላከያ ፓትሮል መኪና ሙሉ በሙሉ መውደሙንና ከጎኑ ቆመው በነበሩ መኪኖች ላይም ጉዳት መድረሱን አርበኞች ግንቦት 7 ባለፈው አርብ የላከልን መረጃ ያመለክታል። ሆቴሉ የመንግስት እና የመከላከያ ባለስልጣናት የሚዝናኑበት ቦታ እንደነበርም ንቅናቄው የላከው መረጃ ያስረዳል።