(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 12/2011) በራያ አላማጣ በትላንትናው ዕለት የተገደሉ አምስት ሰዎች የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ።
በቆቦ፣ ዋጃና ጥሙጋ በተቃውሞ የተዘጉ መንገዶችን ለማስከፈት በመከላከያ ሰራዊት በኩል የተወሰደውን ርምጃን ተከትሎ ግጭት መፈጠሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በትላንቱ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
ተጨማሪ የክልሉ ልዩ ሃይል ወደ አለማጣ ገብቷል። በቆቦም ተቃውሞ ተካሂዷል።
የትግራይ ክልል መንግስት የተገደሉት ሰዎች ሶስት መሆናቸውን አስታውቋል።
ለሟቾች መጽናናትን እመኛለሁ ሲል የገለጸው የትግራይ ክልል መንግስት በጸጥታ አካላት ላይም ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ዕሁድ ዕለት የጀመረው ጥቃት ለሁለተኛ ቀን ቀጥሏል።
የራያ የማንነት ጥያቄ ይመለስ የሚለውን የህዝብ ድምጽ በሃይል ለመቀልበስ የወሰነው የትግራይ ክልላዊ መንግስት በወሰደው እርምጃ ትላንት ብቻ አምስት ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ከሆስፒታሎች በተገኘው መረጃም የትግራይ ክልላዊ መንግስት በወሰደው ርምጃ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥር 35 መድረሱ ታውቋል።ከነዚህ ውስጥም 13ቱ በከባድ መቁሰላቸውን ነው መረጃዎች ያመለከቱት
የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ሰባት እንደሚደርስም አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ይገልጻሉ። ለሁለተኛ ቀን በቀጠለው ተቃውሞ የትግራይ ልዩ ሃይል አቅሙን በማጠናከር ፊት ለፊት በመተኮስ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የመከላከያ ሰራዊት ወደ አላማጣ ቢገባም፡ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት የሚፈጸሙትን ጥቃት ማስቆም እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ዛሬም እንደ ትናንቱ በርካታ ሰዎች በልዩ ሃይል አባላት እየተደበደቡ ነው። የጭስ ቦንቦችም መተኮሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በከተማው ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በዛሬው ዕለት የተገደሉትን ለመቅበር በወጡ የአላማጣ ነዋሪዎችና በትግራይ ልዩ ሃይል መሃል ግጭት መከሰቱን የታወቀ ሲሆን በርካታ ስዎች ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በቀብሩ ስነስርዓት የቤተክርስቲያን ቄሶች እንዳይገኙ በክልሉ መንግስት የደህንነት ሰዎች አማካኝነት ክልከላ ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበረ የገለጹት የኢሳት ምንጮች በህዝቡ ቁጣ መጣሱን ጠቅሰዋል።
ሌሊቱን ቤት ለቤት አፈሳ የተካሄደ ሲሆን በርካታ የአላማጣ ወጣቶች ወዴት እንደተወሰዱ እንደማይታወቅ ነዋሪዎች በስጋት ይናገራሉ።
በዛሬው ዕለት በቆቦ ተመሳሳይ ተቃውሞ የተከሰተ ሲሆን መንገዶች ተዘግተው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቦ መዋሉ ታውቋል።
በዋጃና ጥሙጋም በህዝቡ መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት ለማስከፈት ሞክሯል።
በዚህም ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት መድረሱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መከላከያ ሰራዊቱ ወገንተኝነት ይታይበታል፣ ከትግራይ ክልል ልዩ ሃይል የተሻለ አይደለም የሚለው የነዋሪው ተቃውሞ ጎልቶ እየተሰማ ነው።
በሁለቱ ቀናት ጥቃት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ከ40 በላይ ሰዎች ለተጨማሪ ህክምና ወደ መቀሌ ሆስፒታል እንዲወሰዱ የቀረበውን ማዘዣ እንዳልተቀበሉት የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በአለማጣ የህክምና ማዕከላት የሚገኙት ሰዎች ወልዲያና ደሴ ሆስፒታሎች እንጂ ወደ መቀሌ አንሄድም ማለታቸው ተገልጿል።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት በአላማጣ የተከሰተውን ጥቃት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ሶስት ነው ያለው የክልሉ መንግስት ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ ሲል አስታውቋል።
የህዝብ የማንነት ጥያቄ በማስመሰል ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ተግባር ሲል ያጣጣለው የትግራይ ክልል መንግስት በቀጥታውም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።
የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ከተነሳ ዳግም ጎልቶ ከወጣ ካለፈው ዓመት ወዲህ በትግራይ ክልል ታጣቂዎች በተወሰደ ርምጃ የትላቱን ጨምሮ 10 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ከራያ የፌደራሉ መንግስት ይድረስልን የሚለው ጥሪ ዛሬም ተጠናክሮ እየተሰማ ነው።