በአላማጣ ከተማ የሚካሄደው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ።

በአላማጣ ከተማ የሚካሄደው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ/ም ) ከራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ በሄደ ቁጥር የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት የሚወስዱት እርምጃም በመጠናከሩ ትናንት 5 ሰዎችን ገድለው በርካታ ሰዎችን አቁስለዋል። የራያን የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አግዘው ህዳሩ እርሳቸው ባላቸው መረጃ 9 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በርካቶችም ቆስለዋል። ኢሳት ያነጋገራቸው የከተማዋ ወጣቶች በበኩላቸው ዛሬ የአራት ሰዎች አስከሬን መቀበሩንና የአንደኛው ሰው አስከሬን ወደ ገጠር አካባቢ የሚኖር በመሆኑ ስሙን ለማወቅ አለመቻሉን በመግለጽ የሟቾችን ቁጥር 5 ያደርሱታል። የትግራይ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ 3 ሰዎች ተገድለዋል ብሎአል።
ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የተወሰኑ ሰዎች በክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በርካታ ወጣቶች ደግሞ ከትናንት ምሽት ጀምሮ እስከዛሬ ታፍሰው ተወስደዋል። ግጭቱን ለመከላከል በሚል የመከላከያ ሰራዊት አባለት ወደ ስፍራው ቢገቡም፣ የልዩ ሃይሉ አባላት የሚፈጸሙትን ጥቃት ማስቆም እንዳልቻሉ ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
የትግራይ ኮሚኒኬሽን በመግለጫው የህዝብን የማንነት ጥያቄ በማስመሰል ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ሩጫ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ያለ ሲሆን፣ ለግጭቱ መነሻም በስም ያልጠቀሳቸውን አካሎች ተጠያቂ አድርጓል። አቶ አግዘው ህዳሩ ግን የትግራይ ክልል መግለጫን አጣጥለውታል።
አቶ አግዘው ተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረበለት የፌደራል መንግስት፣ የትግራይ ክልል አስተዳደርን በማማበል ዝምታን መምረጡ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ። በተመሳሳይም የአማራ ክልል አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ነበረበት ሲሉ ይገልጻሉ።