በራያ ህዝብ ላይ የሚደርሱት የመብት ጥሰቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። አሁንም 23 ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ናቸው።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 02 ቀን 2011 ዓ/ም )ካለ ሕዝብ ፈቃድ ከወሎ ክፍለሃገር ተወስዶ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ የተደረጉት ራያዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚያነሱትን የማንነት ጥያቄዎች ለማዳፈን በትግራይ ክልል የሚደርስባቸው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በአዲሱ ዓመት የትምህርት ዘመን ህገ መንግስቱ የሰጠን መብት ይከበርልን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እንድንማር ይፈቀድልን ያሉ 23 ትምህርት ቤቶች በህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት እንደተዘጉ ናቸው። የእነሱን ፈለግ በመከተል ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይዘጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የራያን ህዝብ የማንነት ጥያቄዎች ለማዳፈን በማኅበረሰቡ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ፤ በትግራይ ክልል ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የራያ ተወላጅ የሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጠቀም ማንነት ጥያቄውን በትግራይ ክልል ውስጥ በማድረግ የወረዳ ጥያቄዎችንም ጭምር እንመልሳለን። የሚሉ መረጃዎችን በማሰራጨት የኅብረተሰቡን የማንነት ጥያቄ በልዩ ዞን ለማስመሰልና ጥያቄውን ለማፈን ሙከራ እየተደረገ ነው።
የኅብረተሰቡ ጥያቄ በትግራይ ክልል ውስጥ የልዩ ዞንና የወረዳ ጥያቄ ሳይሆን፤ የማንነት ጥያቄው በታሪክም፣ በትውልድም፣ በስነልቦናም፣ ከምንተሳሰረው ህዝብ ጋር የመኖር ጥያቄ ነው። የልዩ ዞን በትግራይ ክልል ተመለሰ አልተመለሰ ኅብረተሰቡ በዛ አይስማማም። በምንም ዓይነት በየትኛውም አስተዳደር ቢሆን በምንም መስፈርት በየትኛውም ዓይነት የአስተዳደር እርከን ከዛ ክልል ጋር የመኖር ጥያቄ ሳይሆን ከማንነቱ ጋር ከሚተሳሰረው የወሎ ህዝብ ጋር የመቀላቀል ጥያቄ መሆኑን የራያ ሕዝብ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አገዘው ሕዳሩ አስታውቀዋል።