በረከት ስምዖን ህወሃትን ለመታደግ እየተንቀሳቀሱ ነው ተባለ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) ዶ/ር አብይ አህመድ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መመረጡን ያልተቀበሉት አቶ በረከት ስምዖን፣ ከህወሃት ጋር በመሆን የእነ ዶ/ር አብይንና ለማን ቡድን ለመምታት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል። በኢሃዴግ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት እየተመናመነ የመጣው አቶ በረከት፣ በድርጅት አባልነት ከተመዘገቡበት ብአዴን ይልቅ ከህወሃት ጋር ጥምረት በመፍጠር እርሳቸውና በህወሃት ዙሪያ የሚገኙ ጓደኞቻቸው የሚቆጣጠሩትን ስርዓት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ከህወሃት በስተቀር የሌሎች ድርጅቶች ነባር ታጋዮችን ድጋፍ ለማገኘት ባለመቻላቸው ሙከራው ሁሉ እየከሸፈበቸው ነው።
ስልጣናን መልሶ የሚቆጣጠርበት መንገድ ለመተለም የተለያዩ አማራጮችን እያየ ያለው ህወሃት፣ በብአዴን ውስጥ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ የመጣውን አቶ በረከትን ፊት በማሰለፍ የ27 አመታት የበላይነቱን ለማስጠበቅ እንደ አንድ አማራጭ ወስዶታል። አቶ አባዱላ ገመዳ የጠ/ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሆነው በመሾማቸው ህወሃት በእርሳቸው በኩል ሊጫወት ያዘጋጀውን ካርድ እንደተበላ የሚገልጹት የኦህዴድ ምንጮች፣ አቶ በረከት ስምዖን ቀጣዩን ሂደት እንዲጫወትላቸው እያዘጋጁት ቢሆንም፣ እቅዳቸው ለውጥ በሚሹ የኢህአዴግ አባላት አስቀድሞ በመታወቁ እየከሸፈ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ህወሃት በኢትዮ-ሶማሊ ክልል መሪ በኩል ሊፈጥር ያሰበውን ጫና የተረዱት ኦህዴዶች፣ ከሶማሊ ክልል ጋር ያለውን ጉዳይ አለሳልሰው በመያዝ ለህወሃት መግቢያ እንዳሳጡትም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።