የህወሃት ጄኔራሎች የኢትዮ-ሶማሊ ክልል የአገር ሽማግሌዎችን እያስፈራሩ ነው

የህወሃት ጄኔራሎች የኢትዮ-ሶማሊ ክልል የአገር ሽማግሌዎችን እያስፈራሩ ነው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ/ም) አቶ አብዲ ኢሌ በኢትዮ-ሶማሊ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ለከት የለሽ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም፣ የፕሬዚዳንቱን ከስልጣን መነሳት ለመጠየቅ ከክልሉና ከውጭ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን፣ አቤቱታቸውን ለፌደራል ባለስልጣናት ለማቅረብ አዲስ አበባ መገኘታቸውን ተከትሎ የህወሃት ጄኔራሎችና ነባር የድርጅቱ አመራሮች ወደ አገር ሽማግሌዎች ቤት በመሄድ ዛቻና ማስፈራሪያ እያስተላለፉ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።
ሁለት የህወሃት ጄኔራሎቹ ወደ አገር ሽማግሌዎች በመሄድ ከአቶ አብዲ ጋር እንደሚሸመግሉዋቸው ገልጸውላቸዋል። አቶ ስብሃት ነጋና አባይ ጸሃየም እንዲሁ የአገር ሽማግሌዎችን ከአቶ አብዲ ጋር ለማስታረቅ ሲመላለሱ ሰንብተዋል። ይሁን እንጅ የአገር ሽማግሌዎቹ የሽምግልና ጥሪውን ውድቅ አድርገው በአዲስ አበባ መቆየትም መርጠዋል። ይህን ተከትሎ የምስራቅ እዝ ሃላፊ ጄ/ል ማሾ በየነና ሌሎችም ጄኔራሎች ስልክ በመደወል አስፈራርተዋቸዋል።
ምንጮች እንደሚሉት የህወሃት ጄኔራሎች፣ ሶማሊዎችን “ ከአብዲ ኢሌ ጎን በመቆም የኦሮሞን ወይም የኦህዴድን ጥቃት መመከት ትችላላችሁ” እያሉ ለማግባባት ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። አቶ አብዲ አሌ፣ ዱልሚዲድ እየተባሉ የሚጠሩ የአብዲ ኢሌን አገዛዝ ለመቃወም በውጭ አገር የተደራጁ የክልሉን ነዋሪዎችና የአገር ሽማግሌዎችን ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ እያሴሩብኝ ያሉት አክራሪ የኦነግ አባላት ናቸው በማለት በጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና በአቶ ለማ መገርሳ ላይ ክስ እያሰማ ነው። እነዚህ ሃይሎች አብዲ ኢሌን ከስልጣን ለማስወገድ የሚሞክሩ ከሆነ ክልሉን እንደሚገነጥል እየዛተ የሚገኘው አብዲ አሌ፣ እርሱ ያዘጋጃቸው ወጣቶች በሚዲያ ላይ እየወጡ ድጋፋቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም አዲሱን ጠ/ሚኒስትር በኦነግነት እንዲፈርጁ እያሰማራ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ከአብዲ አሌ ውጭ ክልሉን የሚመራ ሰው እንደማይኖር፣ ለአብዲ አሌ አስፈላጊውን መስዋትነት እንደሚከፍሉ በቪዲዮ እየተቀረጹ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ነው፤፡
አብዲ አሌ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ምሁራን፣ ነጋዴዎችና ታዋቂ ሰዎችን እያፈነ ወደ እስር ቤት በመውሰድ ስቃይ እየፈጸመባቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
በእስር ላይ ከሚገኙት ተዋቂ ሰዎች መካከል ዶ/ር ሃሰን አብዲላሂ ዋዴ አንዱ ሲሆኑ እርሳቸው በውጭ አገር የሚኖሩት አጎታቸው ዱል ሚድድ ወይም ለፍትህ መቆም የተባለውን በክልሉ ተወላጆች የተቋቋመውን ድርጅት ይመራሉ በሚል በአቶ አብዲ ኢሌ ትዕዛዝ ታስረው በእስር ቤት እየተሰቃዩ ነው። አብዲ አሌ ለኢትዮጵያ አንድነትና ስልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት የሚታወቀውን የአብዲላሂ ዋዴ ቤተሰቦችን ለማጥፋት ዘመቻ መጀመሩን ምንጮች ይናገራሉ። የአብዲላሂ ዋዴ ቤተሰብ አባላት የንግድ ድርጅቶች በአብዲ ኢሌ ትዕዛዝ የታሸጉና የተወሰዱባቸው ሲሆን፣ አንዳንድ የቤተሰብ ለህይወታቸው በመስጋት ክልሉን ለቀው ወጥተዋል።