ታኀሳስ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የውጥረቱ መካረር ምክንያት የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ከቦርዱ ውሳኔ ቀድመው ወደ ድርጅት ሚዲያ በመሄድ ” አንድነትና መኢአድ የውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ በምርጫ ላይሳተፉ ይችላሉ” የሚል መግለጫ መስጠታቸው ነው።
ዶክተር አዲሱ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች በህገ- ደንባቸው መሰረት ውስጣዊ ችግራቸውን እንዲፈቱ በቦርዱ ቢነገራቸውም ችግራቸውን አለመፍታታቸውን በመጥቀስ፤ አሁን ባሉበት ሁኔታ በምርጫ ሊሳተፉ እንደማይችሉ ነው ያሳወቁት። “መስመሩን ያልጠበቀ ነው”ያለው የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ መግለጫ ያስቆጣው አንድነት ፓርቲ ትናንት ለኢሳት በሰጠው ምላሽ፤ ፓርቲው ምንም ያልፈታው ችግር እንደሌለ በመጥቀስ፤ ቦርዱ በምርጫው እንዳልሳተፍ ካገደኝ፤ ተመጣጣኝ የሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመወሰን እገደዳለሁ ማለቱ ይታወሳል።
ቦርዱ እንዳንሳተፍ ከከለከለን ምንም የሚያደናገጠን ነገር የለም፤እንደውም ቀጥታ ህዝቡን ወደማደራጀትና ወደማታገል እንድንገባ መንገዱን ነው የሚያቀልልን ” ነው ያሉት አቶ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት አቶ አስራት አብርሐ። ዛሬ የድርጅቱ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለ<<ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ >> በሚል ርእስ ባስነበቡት ጽሁፍ -ሁሉን ነገር በደንብና በመርህ የምንሰራዉ፣ ለኢህኣዲግ/ምርጫ ቦርድ ካለን ፍርሃት ሳይሆን ለወደፊቱ ለምናስተዳድረዉ ህዝባችንና ለኢትዮጵያችን ፖለቲካ ክብር ስንል ነዉ፡፡>>ብለዋል። <<ከደንብ ወጥተን የሰራነዉ ክዋኔም ሆነ በግፍ የገፋነዉ አመራርና አባልም የለም፡፡>>ሲሉም ተቀዳሚ ጸሀፊው ገልጸዋል።
በምርጫ ለመሳተፍ ከምር የወሰንነው ምርጫ ቅንጦት ሆኖብን፤ <<የተከበሩ >>እየተባሉ ለመጠራት ሳይሆን እፊታችን ላይ ያለ እድልና ስልትም ስለሆነ ነው>>ያሉት አቶ ተክሌ፤ ኢህአዴግ ደግሞ ማበላሸቱን ተያያይዞትል፡፡>>ሲሉ በምርጫ ቦርድ አካሄድ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ በመጨረሻም፦<< የአንድነት ኣባላት በያለንበት ድርብ ሃላፊነት አለብን፡፡ለአንድነት ሃይሎች ስልቶቻችንን ሁሉ በማቀራረብ የተጀመረዉ የስልጣን ሃይሎችን እያራገፉ ትግሉን በሰለጠነና አንድነቱን በጠበቀ መልኩ የማስቀጠልና፣ ልዩነቶችን በማቻቻል ሰፊ መሰረት የማንበር ሃለፊነት አለብን፡፡ ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ፤ፊታችንን ወደ ዋናዉ ግብ እናድርግ፤ከሃዲዱ አንወርድም!>>ሲሉ ለፓርቲው አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ና ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፦”ጎበዝ ጠንከር ነው”በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፦<<ምርጫ ቦርድ በማንም ታዞም ይሁን አለያም በግል ተነሳሽነት ፤ እያደረገ ያለው ነገር የኢትዮጵያን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከምን ጊዜውም በለይ ወደኋላ ለመመለስ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳው ይገባል፡፡>>ብለዋል። << ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲያሰተዳድር በተሰጠው ኃላፊነት የፓርቲዎች አስተዳደሪ ለመሆን እየቃጣው ያለ ተቋም ነው፡፡>>ያሉት አቶ ግርማ፤ << ቦርዱ ስናከብረው ለመከበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለዚህ ተቋም መጠናክር የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን የተነሳን ፓርቲዎችን ጭምር እየገፋ፤ አለቆቹን ለማስደሰት ተግቶ እየሰራ ይገኛል >>ብለዋል።
<<ለመማር ያልተፈጠረን ሁሉ ምንም ማድረግ ይቻላል? ያሉት አቶ ግርማ፤ <<ማንም ተላላኪና -ላኪ ሆኖ ቢያገለግልም ፤ዛሬ የተሰማኝ ግን -አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን፤ እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በምን ያህል ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ እንደሆኑ ነው፡፡>> ብለዋል።
<< አሁንም ትግሉ መራራ፣ የሚያስከፍለው መስዋህትነትም ውድ ሊሆን እንኳን ቢችል የአንድነት አባላት በድል እንደሚወጡት ምንም ጥርጥር የለኝም>> ያሉት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ <<እሩቅ እንደሆነ አውቀን ለጀመርነው ትግል አቋራጭ እንደማንፈልግ መግለፅ ይኖርብናል>>ብለዋል።
ምክትል ሊቀወ-መንበሩ ሲያጠቃልሉም፦<<ውድ የአንድነት አባላት፣ በቀጣይ አንድነትን- ከምርጫ ቦርድ አሻጥር ለማላቀቅ ለምናደርገው ትግል ቀበቶ ጠበቅ ነው፡፡ ከሰማይ በታች አንድነት ለመፍታት የማይችለውን ፈታኝ ነገር ፤ምርጫ ቦርድም ሆነ በውሰጥችን ያሉት ዙዞምቢዎች ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ጎበዝ ጠንከር ነው፡፡>>ብለዋል። የቦርዱና የፓርቲዎቹ ውጥረት ወዴት ያመራ ይሆን የሚለው ከወዲሁ ብዙዎችን ማነጋገር ጀምሯል።