ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። >> ነው ሲል ግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና ለነፃነት ንቅናቄ ገለጸ።

ታኀሳስ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግንቦት 7 <<ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን!!!>> በሚል ርእስ ዛሬ ታህሳስ 29 ቀን ባስነበበው ርእሰ-አንቀጽ፤በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ እሁድ እለት በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ በግፍ እስር ላይ የሚገኘውን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለ 10 ደቂቃ አቅርቦት እንደነበር በማውሳት፤ይህ የ10 ደቂቃዎች ምስል ለቁጥር በሚያታክት ሁኔታ ተቆራርጦ የተቀጣጠለ በመሆኑና አቶ አንዳርጋቸው በትክክል ምን እንዳለ የሚያስረዳ ባለመሆኑ፤ በይዘቱ ላይ አስተያዬት መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል።

ከዚያ ይልቅ ህወሀት አንዳርጋቸውን ለምን አሁን ሊያቀርበው ፈለገ?የሚለውን ነጠብ ማዬት እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ግንቦት 7፤ ህወሀት በውስጥም፣በውጪም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገባበት ወቅት በመሆኑ በተለይ ውስጣዊ ውጥረቱን ለማስተንፈስና አቅጣጫ ለማስቀየር አንዳርጋቸውን በተቆተራረጠ ምስልና ድምጽ አጅቦ ማቅረቡን ጠቅሷል። <<የህወሓት ሌላው መተማመኛው የጦር ሠራዊቱ ነበር።>>ያለው ግንቦት 7፤ ህወሓት፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ጦር ሠራዊት ዘረኛ በሆነ መንገድ አደራጅና  ከፍተኛ አመራሩን በታማኝ አባላቱ ሞልቶ ተደላድሎ  የተቀመጠ መስሎ ቢቆይም አሁን ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ህወሓትን የማገልገል ፍላጎት እንደሌላቸውና  ይልቁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም የህወሓትን ውድቀት ለማፋጠን ያላቸውን ጉጉት በግልጽ እያሳዩ መሆናቸውን መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አብራርቷል።

እንደ አየር ኃይል ተቃውሞ ገሀድ የወጣ ዜና አይሁን እንጂ በሌሎችም የሠራዊቱ ክንፎች ያለው አመጽ ተመሳሳይ የጡዘት ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጸው ግንቦት 7፤ብአዴን እና ኦህዴድ ውስጥም  ለአገራቸው ለኢትዮጵያ እና እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ እና ለራሳቸው ክብር ያላቸው አባላት ብቅ ብቅ እያሉ ነው ብሏል። እነኚህንና ሌሎችንም በመላ ሀገሪቱ የተቀጣጠሉትን የመብት ጥያቄዎችና አመጾች የተነተነው ግንቦት 7፤ <<ተቃውሞዎችና አመጾች ተቀናጅተው የመጡ ዕለት መድረሻ እንደሚያጣ የተገነዘበው ህወሓት ትኩረት ለማስቀየስ ሲል አቶ አንዳርጋቸውን እንዳቀረበው ገልጿል።

የፊልሙ ማጀቢያዎች የነበሩት የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፓርት፣ ስለእንግሊዝ ጋዜጣ የተነገረው፣ አሜሪካ ስለምትፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተዘከረው ሁሉ የሚያመላክቱት አንድ አቢይ ሀቅ አለ።>>ያለው ንቅናቄው፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን ፀሐይና ብርድ ሳይበግራቸው “እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” እያሉ በእንግሊዝ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች እና በአውሮፓ ኅብረት ሲያደርጓቸው የቆዩ ተቃውሞዎች ውጤታማ መሆናቸውን ነው ብሏል። <<ኢትዮጵያዊያን አንዳርጋቸውን ሲያዩ የሚታያቸው ጽናት፣ አርበኝነትና አልበገር ባይነት ነው። የአንዳርጋቸው ምስል በታየ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ፀጉራቸው ይቆማል፤ ደማቸው ይፈላል።>> ያለው ግንቦት 7፤  ወያኔዎች  አንዳርጋቸውን ወደፊትም እንዲሁ  ሊናገር ያልፈለገውን   ቢያናግሩት የሚፈጠር  ምንም ለውጥ  እንደሌለ አስምሮበታል።

<< እንኳንስ እነሱ አሳሪዎቹ  እሱም ራሱ  በማይገባው መንገድ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ገብቷል።>> ያለው ግንቦት 7፤<< አንዳርጋቸውን ስናይ በህወሓት ፋሽስታዊ መዳፍ ውስጥ የወደቁብንን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ  ጀግኖቻችንን ሁሉ ያስታውሰናል። ያነቃናል፣ ያነሳሳናል!!!”ብሏል። ንቅናቄው በመጨረሻም _<<አንዳርጋቸው ጽጌን፣ በርካታ ጀግኖቻችንን፣እራሳችንንና አገራችንን ከወያኔ እስር ነፃ ለማውጣት ክንዳችንን እናበርታ፤ ሁላችንም “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነን” እንበል፤ ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን እንሁን >>ሲል ለ ኢት ጰያ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።