በሚኒስትር ማእረግ የሚለው ሹመት ውዝግብ እያስነሳ ነው

ህዳር ፲፪(አስ ሁለት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አቶ መላኩ ፈንታ ክሳቸው በየትኛው ፍርድቤት ይታይ የሚለውን ጉዳይ ፥ የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል ለሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ መምራቱ አንዳንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ሹማምንትን እንዳላስደሰተ ታውቋል።

ሰኞ ህዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ አቶ መላኩ ፈንታበሚኒስትር ማዕረግ ተሸመው ሲያገለግሉ እንደነበሩና በወቅቱም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን በመግለፅ በፍርድቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ 25/88 መሰረት እኔ በሚኒስትር ማእረግ የተሾምኩ ስለሆነ ፥ ጉዳዩ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው ሊታይ የሚገባው በማለት መከራከሪያ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኮሚሽኑ አቃቤ ህግም በሚኒስትር ማዕረግ መባላቸው ጥቅማ ጥቅማጥቅሞችን በሚኒስትር ደረጃ እንዲከበርላቸው ተብሎ ነው የሚለውን መከራከሪያና ሌሎችንም በመዘርዘር ተቃውሞ አቅርቦ ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይሆን በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊታይ ይገባዋል ሲል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ችሎቱ በትላንትነው እለት ጉዳዩ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሊያገኝ የሚገባው ነው በማለት ወደዚያው ጉዳዩን በመምራት ለታህሳሱ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሚኒስትር ማዕረግ በሚል በአማካሪ ስም ጭምር ለሚቀመጡ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ሹመት መስጠት የጀመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ሲሆኑ በአቶ ኃይለማርያምም የስልጣን ጊዜ ይህንን ሹመት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግም ጭምር በመስጠት በተለይ በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ በርካታ ሹማምንት እንዲከማቹ ተደርጓል፡፡ ሹመቱ በሚኒስትር ማዕረግ ሲሰጥ አንድ ሚኒስትር የሚያገኘውን ጥቅማጥቅም ከማግኘት ባሻገር በሚኒስትሮች ም/ቤት በአባልነት እንደሚሳተፉ ይታወቃል፡፡ የፌዴራል የስነምግብርና የጸረ ሙስና ዐቃቤ ሕግ ይህ በማዕረግ የተባለው ሹመት የተሠጠው ለጥቅማጥቅም ብቻ ነው ብሎ ክርክር በፍ/ቤት ማቅረቡ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ለሕገመንግስት አጣሪ ጉባዔ መምራቱ አንዳንድ ከፍተኛ ሹማምንትን እንደላስደሰተ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ ትልልቅ ሹማምንት በሚኒስትር ማዕረግ እየተሾሙ ከቀድሞ ሃላፊነታቸው እየተነሱ መሆኑን ያስታወሰው ምንጫችን እነዚህ ጎምቱዎች አንዱ ማባበያ የነበረው የቀድሞ ማዕረጋችሁ ትቀጥላላችሁ መባላቸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህን ማዕረግ ዝቅ የሚያደርግ ክርክር መነሳቱ በቀጣይ የማዕረጉ አስፈላጊነት ጥያቄ ጭምር የሚያስነሳ መሆኑን ጠቅሶ በክርክሩ ጥቅት የማይባሉ ከፍተኛ ካድሬዎች መበሳጨታቸውን አመልክቶአል፡፡