በመርካቶና አካባቢዋ ግጭት ተነሳ

ሐምሌ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብና በኢህአዴግ መካከል የተፈጠረው የመብት ጥያቄ ውዝግብ ተካሮ  በፖሊሶች ላይ ድንጋይ የወረወሩ ሲሆን የኢህአዴግ መንግሥት የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ኮማንዶ የጥይትና አስለቃሽ ጭስ ምላሸ የሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በርካታ ሰዎች የመፈንከት፣ የመደብደብ እና በትልልቅ ኦራል ካሚዮን እየተጫኑ ለጊዜው ወዳልታወቀ ሥፍራ መወሰዳቸውን ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡ በግጭቱ ላይ በመርካቶ አንዋር መስኪድ ዙሪያ፣ አዲስ ከተማ፣ ጨው በረንዳ፣ ኳስ ሜዳ፣ መሳለሚያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአመጹ ውስጥ በመሳተፈቸው ወደ አጠቃላይ የዜጎች የመብት ጥያቄ ያመራ ሲሆን 7፡00 ሰዓት ላይ የጀመረው አመጽ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ ለጊዜው የበረደ ይመስላል፡፡

ዘጋቢያችን በኮንትራት ታክሲ መርካቶ የሚገኘውን አንዋር መስኪድ እና ፒያሳ የሚገኘውን በኒ /ኑር/ መስኪድ ተዘዋውሮ ለመመለክተ የሞከረ ሲሆን የመስኪዶች አቅራቢያ መንገዶች በፌዴራል ፖሊስ በመዘጋታቸው በቅርበት መመልከት አልቻለም፡፡

ይሁን እንጂ በእግሩ በመዘዋወር የመስኪዱን ዙሪያ-ገባ ብቻ እንደተመለከተው ዝንጉርጉሩን የፌዴራል የደንብ ልብስ የለበሱ ትግርኛ ተናጋሪ ልዩ ኮማንዶች የጭንቅላት ሄልሜት፣ በቡትስ ጫማ ላይ የእግር ጋምባሌ የደረቡ፣ የደረትና ትከሻ መከላከያ ልብስ እና የድንጋይ መከላከያ የፕላስቲክ ጋሻ ያነገቡ ልዩ ኃይሎች በትግርኛ- አማርኛ ህዝቡን እያመናጨቁ ቶሎ- ቶሎ እንዲራመድ ሲያዙት አስተውሏል፡፡

ዘጋቢያችን ራጉኤል ቤተክርስቲያን ዙሪያ በሚገኙ ይርጋ ኃይሌ የገበያ ማዕከል ህንፃ፣ ተስፋ ዓለም ሆቴል ህንፃ፣ ንግድ ባንክ ህንፃ፣ እና ፋሲካ ሆቴል ጣራ ላይ መገናኛ ራዲዮ ያያዙ ሲቭል ለባሽ ኃይሎች ተመልክቷል።

በደጃች ዑመር ሰመተር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ልዩ ኃይሎቹ ጊዜያዊ ጣቢያ አቋቁመው የሚያፍሷቸውን ሰዎች በት/ቤቱ እና በአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ በማከማቸት፣ ለ 7ተኛ ጊዜ በኦራል መኪና ጭነው ለጊዜው ወዳልታወቀ ሥፍር ሲወስዷቸው እንዲሁም በአንዋር መስኪድ ዋናው መንገድ ፖሊስ ያንበረከካቸውን እና ያስቀመጣቸውን በርካታ ሰዎች ተመልክቷል፡፡

ዘጋቢያችን ከሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ እስከ ወለጋ ሆቴል አብሮት በእግር የተጓዘ ረዘም ያለ ፂማም ሙስሊም ወጣት ልዩ ኃይሎች በትግርኛ አማርኛ አመናጭቀው በመጥራት ወደ 4ተኛ ፖሊስ ጣቢያ መንገድ ሲወስዱት ተመልክቷል።

ዝናቡ ሲያባራ ቅኝቱን የቀጠለው ዘጋቢያችን በመርካቶ የሚገኙ የአገልግሎት ሱቆች፣ ተቋማት እና ቤቶች ሁሉ ተዘግተው እሁድ ወይም የበዓላት ቀን መምሰሉን ዘግቧል። በታርጋ ቁጥሩ 1911 በሆነ በፖሊስ ኦራል እና በታርጋ ቁጥሩ0059 በሆነ በፌዴራል ላንድ ክሩዘር መኪኖች በርካታ ሰዎች ተጭነው ሲሄዱ ተመልክቷል፡፡

በመርካቶ፣ ፒያሳ አትክልት ተራ፣ ኳስ ሜዳ፣ አብነት፣ መሳለሚያ፣ ጨው በረንዳ፣ ጎጃም በረንዳ እና አሜሪካን ጊቢ አካባቢዎች በቁጥር የበረከቱ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወጣቶችና ጎልማሶች በዝምታ ተሰብስበው ይታያሉ፡፡

የአፍሪቃ ትልቁ ገበያም ዙሪያ ገባው በፌዴራል ኦራል መኪና መንገዱ ተዘግቶና ሱቆችና የንግድ ተቋማት ተዘግተው የጦርነት ቀጠና መስሏል፡፡ የፖሊስ አባላትም የህንፃ ዙሪያ እና አስፋልት ዳር ይዘው የተፋጠጡ ሲሆን ሁኔታው ወደምን ደረጃ እንደሚሄድ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

በህዝብ ሃብት የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ ድርጅት በመኪና በመዘዋወር ለመቅረጽና ምልምል ሰዎችንም ሲያነጋግር ዘጋቢያችን አስተውሎታል፡፡

የረመዳን ፆምን በመፆም ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ካለፉት 8 ወራት ጀምረው በተቀናጀ መንገድ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን ሲሉ በአወሊያ መስኪድ በመሰባሰብ የተቃወሙ ድምጽ ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለሊት ፖሊስ መስኪዱን በኃይል ሰብሮ በመግባት የጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ ካከናወነ በኋላ የደህንነት ኃይሎች የኮሚቴ አመራሮችን በፆሙ ዋዜማና በፆም ጊዜ በማስፈራራትና በማሰር መቅጣት መጀመራቸው ያስቆጣቸው ሙስሊሞች ፣ ትላንት ዓርብ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆነው በዝምታ ሠላማዊ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

ዛሬ ከእኩለ ቀን ጀምሮ በአንዋርና ፒያሳ በኒ /ኑር/ መስኪድ በመሰባሰብ ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ሙስሊሞች ፣  የኮሚቴ አባላቶቻቸውና ሙስሊም ጋዜጠኞች የሆኑት አክመል ነጋሽ፣ ኤሊያስ እሸቱ፣ ፣  ዩሱፍ ጌታቸው ቤታቸው እየተበረበረ እንደሆነና መታሰራቸውን በመስማታቸው ሁኔታው ወደ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሸጋግሯል ሲሉ ለደህንነታቸው ሲሉ ሥማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሙስሊም ማህበረሰቡ ተወካይ ገልጸውልናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውንና በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ያሰራቸውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ ዳኢዎችና ሙስሊም ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት አቅርቦ በሽብርተኝነት ክሥ መሥርቶ የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፖሊስ እንዲጠይቅባቸው አድርጎ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት መልሷቸዋል።

በእሥር ላይ ከሚገኙት የኮሚቴ አባላት ውስጥ ትናንት በአራዳ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ሸህ መከተ ሙሄ፣ ጀማል ያሲን፣ ሱልጣን አማን፣ የሙስሊም ጉዳይ መጽሔት አዘጋጅ ዩሱፍ ጌታቸው እና ዑስታዝ ኑሩ ቱርኪ ይገኙበታል፡፡

ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ትላንት ማታ መኖሪያ ቤቱ በፖሊስ የተበረበረ ሲሆን የእርሱ፣ የሚስቱን እና የሚስቱን እህት ሞባይል ስልክ፣ ዶክመንቶችና ሌሎች ንብረቶች ከወሰዱ በሁዋላ እርሱን ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ወስደው አስረውታል።

በድሬዳዋ ደግሞ ሙስሊሞች የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ ወደ መስኪዶች ሄደው ከሰገዱ በሁዋላ ወዲያውኑ መስጊዶችን ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ሙስሊሞቹ በአንድነት ሆነው እንዳይቆሙ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። አንድ የአይን እማኝ እንደተናገረው፣ በእርሱ እድሜ ፌደራል ፖሊስ ቆሞ ህዝቡን ሲያስጸልይና በቃችሁ ብሎ ሲያባርር ሲመለከት ይህ የመጀመሪያው ነው።

በመንግስት እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል ያለው ፍጥጫ በየጊዜው እየተካረረ በመሄድ ላይ ነው። ሙስሊሞች ያነሱዋቸው ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ተቃውሞአችንን እንደማይተው፣ መሪዎቻቸው ቢታሰሩም ትግሉን እንደማያቋርጡ እየተናገሩ ነው። መንግስት በበኩሉ የሙስሊሙ ጥያቄ የተፈታ በመሆኑ፣ ተቃውሞው መቆም አለበት ይላል።

የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ ጊዜያዊ አመራሩን የተረከቡት ባለስልጣናት የሚከተሉት መስመር አቶ መለስ ይከተሉት ከነበረው የተለየ እንደማይሆን እያመላከተ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል። ኢትዮጵያውያን ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ግራ መጋባታቸውን በክልሎች የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን እየገለጡ ነው። ጭንቀቱ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ ጎልቶ የሚታይ ሆኗል። በአቶ በረከት ስምኦን የሚመራው ብአዴን ሼክ አልአሙዲንን ከጎኑ በማሰለፍ የስልጣን መደላድሉን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ህዝቡ  ተቃዋሚዎች ወደ አንድነት በመምጣትና አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት እንዲያወጡዋት ከፍተኛ ተስፋ መጣሉንም ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል።

መልካም ነገር ይመጣል ብሎ  ተስፋ የሚያድርገው ህዝብ ብዙ ቢሆንም፣ ከዚህ የባሰም ሊመታ ይችላል ብሎ የሚሰጋው ህዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide