ፍትህ ጋዜጣን ማገድ የአገሪቱ ሁኔታ ወደ አደገኛ ሁኔታ መሄዱን የሚያመላክት ነው ሲል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተናገረ

ሐምሌ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ ይህን የተናገረው ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ነው።

መንግሥታዊው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ሃሙስ ምሽት ሳንሱር አድርጎ አላትምም ብሎ ያቋረጠውን የፍትህ ጋዜጣ ቅጽ 5 ቁጥር 197 ፣ ከፌዴራል ጸረ ሽብር ግብረይል፣ ዐቃቤ- ሕግ፣ የደህንነት ኃይሎች እና ከፍትህ ሚንስትር ተወካዮች ጋር ከተነጋገረና ይዘቱን ካስገመገመ በኋላ ትላንት ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ላይ በደህንነት ኃይሎች ቅርብ ክትትል ሥር ሆኖ ጋዜጣው እንዲታተም ቢፈቅድም ፣ በዛሬው ማለዳ ለሥርጭት እንዳይውል አድርጓል።

በትላንትናው ዕለት ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት መጥተው ጋዜጣውን ሣንሱር ሲያደርጉ የነበሩት ዐቃቤ- ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ፣ ምክትል የፍትህ ሚንስትር  አቶ መሐመድ አባጊሳ እና ሌሎች ሹመኞች በጋዜጣው አዘጋጆች ላይ የስነልቦና ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል።

በዛሬው ዕለት ለገበያ የሚቀርቡት አዲስ አድማስ፣ ነጋድራስ፣ ኢትዮ ቻናል እና ሌሎች ጋዜጦች በጥብቅ ፍተሻ ሥር ውለው ለሥርጭት እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን ሁኔታው ግራ ያጋባው አንድ ጋዜጣ ተረካቢ ዛሬ ምን የተለየ ነገር ኖሮ ነው ሲል የጸጥታ አስተናባሪውን ሲጠይቀው፣  የፍትህ ጋዜጣ ዕትም እንዳይወጣ ነው፣ በድጋሚ ህትመቱ እንዲቀጥል ሲፈቀድ የተበላሹ የጋዜጣው ቅፆችም የትም እንዳይወጡና እንዳይቀላቀሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር ብሎ መልሶለታል፡፡

ፍትህ ጋዜጣ ሃሙስ ጠዋት ለብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት የሠላሳ ሺህ ኮፒ የሕትመት ዋጋ ወደ ሰማንያ … ሺህ ብር የከፈለ ሲሆን ማተሚያ ቤቱ ሃሙስ ማታ እንደ ውሉ ማተም ሲገባው ፕሌት አልቆብኛል የሚል ምክንያት በማቅረብ የፍትህን ጋዜጣ ህትመት አቋርጦ አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ አል አልመን እና በሪሳን አትሞ ጨርሶ ቅዳሜና እሁድ የሚታተሙትን አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር፣ ፎርቱን እና ካፒታልን ሲያትም የፍትህ ጋዜጣ ህትመት ክፍል ክትትል ተመልክቷል፡፡

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝና ባልደረቦቹ በትላንትናው ዕለት ለ1፡30 ደቂቃ ያህል ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽታሁን ዋለ፣ ከህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት እና ከህግ ክፍል ኃላፊ አቶ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ም/ ሥራ አስኪያጁ ፣ ፍትህ ጋዜጣን በዚህ ሁኔታ አናትምም፣ እኛ የመንግሥት ማተሚያ ቤት ነን፣ ብለዋል።

ሃላፊዎች  ” የሽግግር ምክር ቤት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሞቱ ሲል ፣  ቢቢሲ በጸና ታመዋል ይላል፣ አቶ በረከት በበኩላቸው በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው ይላሉ” በማለት የሰራችሁትን የፊት ገጽ ዜና ለማተም አንገደድም በማለት ችግሩ የፕሌት እጥረት ሳይን የሳንሱር ጉዳይ መሆኑን በማመን ለጋዜጣው ሀላፊዎች ተናግረዋል።

የሕግ ክፍል ኃላፊውም ይህ በሀገር ላይ ጉዳት ስለሚያመጣ እና ስለሚያስጠይቀን ነው የማናትመው ሲሉ ፣ ይህን የማድረግ ስልጣን ማን ሰጣችሁ? የሀገሪቱን ሕገ- መንግሥት እየናዳችሁት ነው ? ሲል የጋዜጣው አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አጥተው ማተሚያ ቤቱ ይጠየቅበታል ያሉትን የህግ አንቀጽም ማብራራት ተስኖአቸው ታይተዋል፡፡

የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በበኩሉ ” ዛሬ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ይዛችሁና የህሊናችሁን ወቀሳ ችላ ብላችሁ ፍትህን በመዝጋት ከገዢው ፓርቲ ጋር ተባባሪ አፋኝ መሆን ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ከታሪክ እና የእኛ ትውልድ የሆኑ ልጆቻችሁ በሚፈጥሯት ኢትዮጵያ ላይ የጥቂት አፋኝ ግለሰቦች የሚመሩትን ፓርቲ ለማስደሰት በሚል ሀገር እያፈረሳችሁ ነው፡፡ እናንተ በምን ዓይነት የህግ ሥልጣን ነው አናትምም ያላችሁት” በማለት ጠይቋቸዋል።

የማተሚያ ቤቱ ም/ ሥራ አስኪያጅ ” በዚህ ዓይነት እንዴት ነው የምንነጋገረው፣ በቃ እናንተ በእኛ ለመገልገል ይህን ያህል መብት ማን ሰጣችሁ” ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን ፣ ጋዜጠኛ ተመስገንም ” የመለስ ዜናዊ መሞት አለመሞት  እናንተን በተለይ እንዲህ ሊያስጨንቃችሁና የሀገሪቱን ህዝብ መተንፈሻ ነፃ ጋዜጣ እስከማገድ እርምጃ ሊያስወስድ ይችላል ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ሌላው ይቅርና ሚንሥትር አቶ በረከት ስምዖን የጠ/ሚ መለስን መታመም ባመኑበት በዚህ ወቅት የእናንተ መከራከር ይህን እውነት የሚክድና በሀገሪቱ ተቋማት ላይ እምነት የማልጥልበትን ምክንያቶቼን ይበልጥ አጠናክሮልኛል ” ብሏቸዋል፡፡

ተመስገን እርምጃው አገሪቱ ወደ ባሰ ሁኔታ እየገባች መሆኑን ያመላክታል በማለት ተናግሯል።

በሌላ ዜና ደግሞ ቄራ የሚገኘው የኦራይዘን ማተሚያ ቤት ባለቤት አቶ የሺጥላ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ፖሊስ እንዳሰራቸው ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ እናቀርባለን

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide