አቶ አባዱላ ገመዳ የዘንድሮ ፓርላማ መራዘም ከጠ/ሚኒስትሩ ሕመም ጋር አይያያዝም አሉ

ሐምሌ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰኔ 30 መዘጋት የነበረበት የዘንድሮ ፓርላማ የሥራ ፕሮግራም መራዘም እንዲያው ልማድ ሆኖ እንጂ ከጠ/ሚኒስትር መለስ ሕመም ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ነገር የለም ሲሉ አቶ አባዱላ ገመዳ ገለጹ፡፡
የፓርላማው አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ዛሬ በጽ/ቤታቸው የፓርላማውን ዓመታዊ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ የፓርላማው የስራ ጊዜ መራዘም ከጠ/ሚኒስትሩ ጤንነት ጋር ይያያዝ እንደሆን ከጋዜጠኞች ተጠይቀዋል፡፡

እሳቸውም በሰጡት ምላሸ ሰኔ 30 መዘጋት የነበረበት ፓርላማ በአንድ ሳምንት የተራዘመው
በሕገመንግስቱ መሰረት አስቸኳይ ስብሰባ አፈጉባኤው የመጥራት ሥልጣን ስላለው ነው፡፡

የተጠራበት ምክንያትም የ2005 በጀት ብዙ ስለነበርና ቋሚ ኮሚቴው የሚመለከታቸውን ለማወያየት ጊዜ በመውሰዱና አንዳንድ አጣዳፊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ሕጎች በመምጣታቸው ነው ብለዋል፡፡

አጣዳፊ ካሉት ውስጥ ከሰኔ 30 በኃላ 600 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት መምጣቱን ፣ስምምነቱ እስከ መስከረም መጨረሻ ም/ቤቱ እስኪከፈት ይጠብቅ የማይባልና ለልማት
አስፈላጊ ስለነበር ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በበጀት መዝጊያ ላይ የጠ/ሚኒስትሩ መገኘት እንዲያው ልምድ ሆኖ እንጂ አንዳችም አስገዳጅ ነገር ኖሮ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ ከበጀት ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ የሚገኙት የበጀት ቅነሳ ሞሸን ሲቀርብ በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ለመስጠት ነው ያሉት አቶ አባዱላ ዘንድሮ የቀረበ የበጀት ቅነሳ ሞሽንም አልነበረም ብለዋል፡፡

የበጀት ጉዳይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ኃላፊነት መሆኑንና ጠ/ሚኒስትሩ ኖሩም አልኖሩም የፓርላማው የሥራ ጊዜ መራዘም ከበጀቱ ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ነገር የለም በማለት ሲቀርቡ የነበሩ አስተያቶችን አስተባብለዋል፡፡
አቶ አባዱላ አያይዘውም ጠ/ሚኒስትሩ ቢገኙም እንኳን ዘንድሮ ፓርላማ በሥራ ብዛት ምክንያት ጊዜው መራዘሙ የማይቀር ነበር በማለት ጉዳዩ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር እንደማይያያዝ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘም ፓርላማው በዓመቱ መጨረሻ ሰኔ ወር በርካታ ሕጎችን በጥድፊያ የሚያጸድቅበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሕጎቹ በሒደት ወራትን ስለሚፈጁ ነው፡፡ለምሳሌ የኢንቨስትመንት ማሻሻያ ሕጉ ስምንት ወራት የሚመለከታቸውን ለማወያየት ጊዜ ወስዶአል ካሉ በኃላ ይህ ሁኔታ እንዲሻሻል ግን ትኩረት ሰጥተን መሥራት እንደሚገባ አምነዋል፡፡
በሰኔ ወር በአንድ የግማሸ ቀን ስብሰባ ብቻ ወሳኝ የሆኑ 12 ያህል አዋጆች ለፓርላማው መቅረባቸው ይታወሳል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide